የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አንድነቱን ማጠናከር አለበት ---አቶ ሽመልስ አብዲሳ

62

አዳማ ግንቦት 9/2011የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አንድነቱን በማጠናከር በፖለቲካ መስክ የተገኘውን ድል በልማትም መድገም እንዳለበት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ።

የአርሲ ዞንና የአሰላ ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ የልማትና የሰላም ኮንፍረንስ  ዛሬ በአሰላ በተካሄደበት ወቅት አቶ ሽመልስ እንዳሉት  ጥቅማቸው የተነካባቸው አፍራሽ ኃይሎች በክልሉ ቦታ የላቸውም።

ህዝቡ  ከምንም በላይ አብሮነቱን  በመጠበቅ  በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ እንዲቀጥል ማስቻል ይጠበቅበታል።

የኦሮሞ ህዝብ በክልሉ ከሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር  አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል በልማቱም መድገም እንዳለበት አሳስበዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ያለውን የገዳ ሥርዓት እሴት ጠብቆ ለሰላምና ልማት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን  ጋር በአንድነት መስራት አለበትም ብለዋል።

ህብረተሰቡን  በኃይማኖት ለማከፋፈልና አንድነቱን ለማዳከም ጽንፈኞች ያደረጉት ሙከራ በህዝቡ አንድነትና ትብብር መክሸፉን ምክትል ፕሬዚደንቱ ገልጸዋል።

ለቤተ እምነትም ሆነ ለህዝባዊ ተቋማት የግንባታ ስራ የሚውል መሬት የመስጠት ኃላፊነት  የመንግስት ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት በየደረጃው የህዝቡን የሰላም፣ ልማት እና የመልካም አስተዳደር  ጥያቄ ለመመለስ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የእስልምናና የክርስትና ኃይማኖት መሪዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ለህዝቦች አንድነት ፣ መቻቻልና መከባበር  መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ህዝብን በመጉዳት ጥፋት የፈጸሙ አካላት ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

ኃይማኖትን  ሽፋን በማድረግ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ ቡድኖችና  ግለሰቦች በእስልምናም ሆነ  በክርስትና በኩል ቦታ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ህዝቡን የሚያጋጭና የሚያበጣብጡ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የህግ የበላይነትመከበር አለበት፤ ህዝቡን የሚያጋጭና የሚያበጣብጥ ሊወገዙና ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል።

መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ በተለይም የወጣቶች የሰራ አጥነት ችግር መፍታትና የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲስተካከል በትኩረት መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።

ከአርሲ ዞን ወረዳዎችና አሰላ  ከተማ አስተዳደር  የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተስብ ክፍሎች በኮንፍረንሱ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም