አሳታፊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለመፍጠር በቅድሚያ ህገ መንግስቱን ማሻሻል ይገባል - ምሁራን

85

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2011በኢትዮጵያ አሳታፊ የፌደራሊዝም ስርዓት ለመፍጠር በቅድሚያ ህገ መንግስቱን ማሻሻል እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚቀርበው የክልል ይገባኛል ጥያቄ በህገ መንግስቱ ላይ ግልጽ የሆነ መስፈርት ባለመኖሩም ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም ጥናት ማዕከል በኢትዮጵያ አማራጭ የፌደራሊዝም ስርዓትና አተገባበር ላይ ያተኮረ ውይይት አዘጋጅቷል።

በውይይቱ"ኢትዮጵያ ምን አይነት የፌደራሊዝም ስርዓት መከተል እንዳለባትና በአተገባበሩ ውስንነቶች  ዙሪያ" ምሁራኑ ምክክር አድርገዋል።

የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው እንዳሉት፤ አሀዳዊ ስርዓትና ብሄር ተኮር ፌዴራሊዝም ከጽንሰ ሃሳብም ባለፈ በተግባር ተፈትነው ውጤታማ አልሆኑም።

በጠቅላይነትም ሆነ ልዩነት ላይ የሚያተኮሩ ሃይሎች ብሄርተኞች በመሆናቸው ሁለቱን ተቃርኖዎች የሚያስታርቅ አሰራር መዘርጋት ይገባል ብለዋል።

የዜጎች በቋንቋ የመደራጀት መብት መከበር እንዳለበት የገለጹት አቶ ልደቱ፤ እንደ አስፈላጊነቱ በከተሞች ላይ አሀዳዊ አሰራር ተግባራዊ ቢደረግ ለኢትዮጵያ አንድነት መልካም መሆኑን አስምረውበታል።

በኢትዮጵያ ዜጎችን አሳታፊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለመገንባት በቅድሚያ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው የፌደራሊዝም ስርዓቱ አንድነትን ከማጥበቅ ይልቅ ማላላትን የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ከኢፌዲሪ ህገ መንግስት የሚቀዳ በመሆኑ በቅድሚያ ህገ መንግስቱ መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል።

ህግ መንግስቱን በማጽደቅ ሂደት የተሳተፉ አካላት የራሳቸውን ሪፐብሊክ አገር ለመመስረት ያለሙ ስለነበሩ ከአንድነት ይልቅ ለመከፋፈል ቅድሚ ሰጥተዋል ሲሉም ተችተዋል።

ለአብነት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ለብሄር ብሄረሰቦች እስከመገንጠል ያጎናጸፋቸው መብት ባይገባ መልካም ነበር ከገባ ደግሞ በቅድመ ሁኔታዎች መታጀብ ነበረበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ማለቂያ የሌለው የክልል እንሁን ጥያቄ በህገ መንግስቱ ላይ በግልጽ የተቀመጠ መስፈርት ካለመኖር የመነጨ መሆኑን ጠቁመዋል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ በማንኛውም ጊዜ ክልል መሆን እንደሚችል ተቀመጧል።

ይህ ደግሞ ከ80 በላይ ክልሎችን የመመስረት በህገ መንግስታዊ መብት እንዲኖራቸው አስችሏል ብለዋል።

በመሆኑም አንድ አካባቢ ወይም ህዝብ ክልል መመስረት ስለፈለገ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ቁጥር፣ በእድገት ተመጣጣኝነት እና ሌሎችም ግልፅ መስፈርቶች ያስፈልጋሉ።

ለዚህ ደግሞ ህገ መንግስቱን ቀድሞ ማሻሻል አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነም ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም