የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከግሎባል አሊያንስ ሊቀመንበር አቶ ታማኝ በየነ ጋር ተወያዩ

68

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን (ግሎባል አሊያንስ) ሊቀ-መንበር አቶ ታማኝ በየነ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያውያን መብት እንዲከበርና ችግር ሲደርስባቸውም ከጎናቸው በመሆን እያደረገ ላለው በጎ ተግባር ማመስገናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

መንግስት ከምንጊዜውም በላይ ዳያስፖራው በአገሪቷ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ተቀራርቦ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ የሆነው የዳያስፖራ ኤጄንሲ ለግሎባል አሊያንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በቅርቡም በጌዲዮ ለተፈናቀሉ ዜጎች ላደረገው ድጋፍና ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ላሳየው አጋርነት አመስግነዋል።

የግሎባል አሊያንስ ሊቀ-መንበር አቶ ታማኝ በየነ በበኩላቸው ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያውያን መብት እንዲከበርና አደጋ ሲደርስባቸውም እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲቀጥል እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኛ የዳያስፖራ አባላትን በማሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሙያቸው የድጋፍና የስልጠና እገዛ እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የግሎባል አሊያንስ የቦርድ አባል አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው በቀጣይ የአሊያንሱን እንቅስቃሴ በማስፋት በተቋማት የአቅም ግንባታና በዴሞክራሲ ማጎልበት ስራዎች ለመሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም