ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነት መግጠም አንፈልግም አሉ

68

ግንቦት 9/2011 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት እንደሌላቸው መናገራቸውን ከዋይትሀውስ ባለስልጣናት የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።

በአሜሪካና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት ሰሞኑን ተባብሷል።

ይህንን ተከትሎ ትራምፕ ከረዳቶቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት አሜሪካ በኢራን ላይ ጦርነት ለመክፈት ግፊት እና ፍላጎት እንደሌላት መናገራቸው ተሰምቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከኢራን ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ የባህረሰላጤው ሀገራትን መሪዎች እያነጋገሩ መሆኑ ነው የተነገረው።

የኢራን ከፍተኛ መሪ አያ ቶላህ ሃምኒ “እኛም ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት የለንም እነሱም አያደርጉትም” ብለዋል።

ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር ውጥረት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የጦር መርከቦችንና ተዋጊ ጄቶችን በባህረሰላጤው አስፍራለች።

በኢራን ጎረቤት በሆነችው ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የዲፕሎማሲ ሰራተኞቿንም ወደ ሀገራቸው እንዲወጡ አድርጋለች።

በሌላ በኩል ኢራን በፋርስ ባህረሰላጤ በሚንቀሳቀሱ ጀልባዎቿ ሚሳኤል በመጫን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬት የባህር ዳርቻ የሚገኙ አራት የነዳጅ ታንከሮችን መክበቧ እየተነገረ ነው።

ቴህራን ግን ስለሁኔታው የማውቀው ነገር የለም፤ የተባለውን አልፈፀምኩም ብላለች።

ምንጭ፦ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም