ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰባት የአፍሪካ አገራት የሚተገበር የግብርና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

214

ግንቦት  9/2011  ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰባት የአፍሪካ አገራት በ34 ሚሊየን የካናዳ ዶላር የሚየተገበር የግብርና ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከተመደበው ጠቅላላ በጀት ሶስት ሚሊዮን ዶላር የምታገኝ መሆኑም ታውቋል።

ፕሮጀክቱ ከካናዳና አውስትራሊያ መንግስታት ጋር በመተባበር የሚተገበር ሲሆን ለቀጣይ 10 ዓመታት የሚቆይ ነው ተብሏል።

መርሃግብሩ ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሲደረግ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የአፍሪካን የግብርና መፃሂ ሂደት በምርምና ጥናት በማገዝና በመደገፍ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ከፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ሶስት ሚሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ጠቅሰው ገንዘቡ ኢትዮጵያ ያላትን የግብርና የምርምር ውጤት ያላለቁትን ለመጨረስና ያለቁትን ድግሞ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቱ በዋናነት በኢትዮጵያ ከሚሰሩት የምርምር ስራዎች በተጓዳኝ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር፣ ሙያተኞችን ለማሰልጠንና ለማስተማር፣ የማዳቀል ስራን ለማዘመን፣ በሰብልና በከብቶች ላይ የሚከሰት በሽታ ለመከላል እንዲሁም የምርምር አቅምን ለማጎልበት ያግዛል።

የኢትዮጵያ መንግስት በግብርናው ዘርፍ የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን ሚና ይጫወታል ብለዋል።


በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ኦንቷዋን ሸቭሪዮ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ካናዳ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ የልማት አጋርነት ያላቸው አገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያ በምታገኝው ድጋፍ እያስመዘገበችው ያለው ውጤት የሚያኮራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለካናዳ በአፍሪካ ቀዳሚ የልማት አጋር እንደሆነች ጠቅሰው አገሪቷ የምታገኛቸውን የልማት ድጋፎች በማቀናጀት፣ በፖሊሲ በማስደገፍና ውይይት በማድረግ የምትሰራው ሥራ በግብርናው መስክ አመርቂ መሆን ችሏል።

ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ዙሪ በአምስት የአፍሪካ አገራት ሲተገበር የቆየ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ማላዊ፣ ሞዛንቢክ፣ ዛንቢያና ዚምባቤ የሚተገበር ይሆናል።


በኢትዮጵያ የሚተገበረው ፕሮጀክት በዋናነት በአየር ንብርት፣ ለሴቶችና ወጣቶች ስራ ለመፍጠር፣ ለምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለውሃ ፖሊሲና ፕሮግራም መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ ይውላል።

በተለይም ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የሚከሰረተውን የማሽላ በሽታ ለመከላከል፣ የእንስሳት ጤናና የምግብ እጥረትን በመከላከል በአስር ዓመታት 60 ሚሊዮን ሰዎችን ያግዛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ፒተር ዶይሊ አገራቸው በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ጋር በደህንነትና መረጋጋት እንዲሁም በኢኮኖሚ አጋርነት እድገት እንዲመዘገብ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

አውስትራሊያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማዕድን፣ በትምህርት፣ በባህልና ግብርና ከአገራቱ ጋር እየሰራች እንደሆነ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ቀርፃ መስሯቷ ለአካባቢ ተጽህኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመፍጠር እንደሚያስችላት ጠቅሰው በዛሬው እለት ይፋ የሆነው ፕሮጀክት ኢትዮጵያን የበለጠ የሚያግዝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በጥናትና ምርምር ላይ መሰረት አድርጎ የአገሪቷን ዜጎች በድርቅ ምክንያት የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን ለመከላከል፣ ገቢን ለማሳደግ፣ ዘላቂ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር፣ የሴቶችና ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ያግዛል ብለዋል።