ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሀብቷ በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም

58

አዲስ አበባ  ግንቦት 9/2011 ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራትም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ አነስተኛ በመሆኑ መሻሻል ይገባዋል ተባለ።

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲሰሩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ውይይት አድርጓል።


ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ወቀት እንዳሉት ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራትም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ አነስተኛ ነው።

ይህን ተከትሎ በሆቴልና ቱሪዝም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየውን ችግር በመፍታት ገቢውን ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት አለባቸው።


በዘርፉ ያለው የሰው ኃይል እጥረት፣ በቂ መረጃ ያለመኖር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለዚህ ተጠቃሽ መሆናቸውንም ተናግረዋል።


በመሆኑም ቱሪዝምን በሰለጠነ የሰው ኃይል መምራት፣ ማዘመን፣ የቱሪዝምን መረጃ በአግባቡ መዝግቦ መያዝ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።


የባለሙያ እጥረቱን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።


በትስስር ከተሰራ ከስራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።


በውይይቱ ላይ የተገኙት የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ መስራት አማራጭ የሌለው መሆኑን ጠቁመዋል።


ከጎንደር የቱሪዝም ኮሌጅ የመጡት አቶ ጋሻው እንዳለው በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።


የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ስልጠና ከሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ትስስር የበለጠ እንዲጠናከር በህግ መታገዝ ያስፈልጋልም ብለዋል።


በከፍተኛ ትምህርት በኩል በዘርፉ ስልጠና የሚሰጡ ኮሌጆች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።


ከደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የመጡት አቶ ዳኜ አራጌ በበኩላቸው ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ሆቴሎች የተማሩ ሰዎችን መቅጠር አለባቸው ብለዋል።


አሁን ላይ የሆቴል ባለቤቶች ዘመዶቻቸውን የሚቀጥሩበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመው በቀጣይ ሊታረም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።


በዘርፉ ስልጠና ከሚሰጥ የግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የመጡት አቶ አህመድ አደም እንዳሉት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከሌሎች አገራት ልምድ በመቅሰም ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል ።


መንግስት የግሉን ዘርፍ የበለጠ በማሳተፍ ለአገሪቱ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማድረግ አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም