አራት ድርጅቶች ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ ተያዙ

144

ግንቦት 8/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በአስመጪና አከፋፋይነት የተሰማሩ አራት ድርጅቶች ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተያዙ።

የከተማዋ ገቢዎች ባለስልጣን የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ታምራት ንጉሴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ትናንት ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገ ክትትል ድርጅቶቹ እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ ተይዘዋል።

ባለስልጣኑ በሴራሚክስ፣ በግራናይትና በባኞ ቤት ዕቃዎች ንግድ ላይ በተሰማሩ ድርጅቶች ላይ ለአንድ ወር ባደረገው ጥናትና ክትትል በቂ አቅርቦት ያላቸው ድርጅቶች ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እንደነበር ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ትላንት ባደረገው የዘመቻ ስራ ድርጅቶቹ ከ100 ሺህ ብር በላይ ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እንደነበር ማረጋገጡን አብራርተዋል።

ህገ ወጥ ግብይት ሲፈጽሙ የተያዙት ድርጅቶች በተለምዶ ካሳንችስና ሲግናል ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን የአብስራ ሴራሚክስ፣ ልዩ አጨራረስ እና ፎዚያ ሴራሚክስ የተባሉት ድርጅቶች በአከፋፋይነት የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን ሳባ ግራናይትና ሴራሚክስ የተባለው ድርጅት ደግሞ በአስመጭነት መስክ የተሰማራ መሆኑን ገልጸዋል።

በህገ ወጥ ድርጊቱ ከተሳተፉት ድርጀቶች ውስጥ የሁለት ድርጅቶች ባለቤቶችና  ስምንት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ህገ ወጥ ድርጊቱ አስተዳደራዊና የወንጀል ቅጣት የሚያስቀጣ ሲሆን  አስተዳደራዊ ቅጣት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲያከናውን የተገኘ ነጋዴ በእያንዳንዱ ሽያጭ እስከ 50 ሺህ ብር እና በወንጀል ደግሞ ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ከ3 እስከ 5 ዓመት ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በታክስ አስተዳደር አዋጁ ተደንግጓል።

የድርጅቶቹ የገቢ ደረጃ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ3 እስከ 7 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ሽያጭ ያሳወቁ ናቸው።

ያለ ደረሰኝ ግብይት ይፈጸምባቸዋል ተብለው ከተለዩ ዘርፎች ውስጥ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት አንዱ ሲሆንበቀጣይም ተመሳሳይ ክትትል በማድረግ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለስልጣኑ አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ቀደም ሲል በብረት ንግድ በተሰማሩ ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ትናንት የወሰደው እርምጃ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም