በአዳማ ከተማ ህገ ወጥ ግንባታን ስርዓት ለማስያዝ ሲሰራ የተከሰተ ግርግር በቁጥጥር ስር ውሏል-- ፖሊስ

62

ግንቦት 8/2011 በአዳማ ከተማ አስተዳደር ገንደሀራ ቀበሌ ህገ ወጥ ግንባታን ስርዓት ከሚያሲያዝ ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ግርግር በማረጋጋት መቆጣጠሩን ፖሊስ አስታወቀ ፡፡

የአስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ዲኖ ይማም ለኢዜአ  እንደገለፁት ዛሬ የቀሰቀሰው ግርግር  ምትክ ቦታ የተሰጣቸው የልማት ተነሺዎች ካርታና የግንባታ ፍቃድ አላገኘንም በሚል  ህገወጥ ቤቶች መገንባታቸው ተከትሎ ስርዓት እንዲይዙ ሲደረግ ነው።

በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ለማፍረስ ወደ ቦታው በተንቀሳቀሰው የፀጥታ ኃይል በማወክ ግርግር ማስነሳታቸውን ተናግረዋል።

ኮማንደሩ እንዳሉት በድርጊቱ የተሳተፉ  አካላት የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር በፀጥታ አካላት  ላይ ድንጋይ በመወርወር ህግ የማሰከበር ሂደቱን ለማስተጓጓል ጥረት አድርገዋል። 

በዚህም በሁለት የፖሊስ  ሞተር ብስክሌቶችና በሌሎችም ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

ፖሊስ የተቀሰቀሰውም ግርግር በማረጋጋት መቆጣጠሩን ያስታወቁት ኮማንደር ዲኖ ችግር  የፈጠሩ ግለሰቦችን መያዛቸውን ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው አስተዳደሩ ባለፉት  ዘጠኝ ወራት አንድ ሺህ ስምንት መቶ በላይ ለሚሆኑ የልማት ተነሸ አርሶ አደሮች እድሜአቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ ከሆኑ ልጆቻቸው ጋር ምትክ ቦታና ለዚህ ህጋዊ ሰነድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ግርግሩ የተነሳው ምትክ ቦታ ያልደረሳቸው እየተሰጠ በሂደት ላይ እያለ በትዕግስት መጠበቅ ካለመቻል እንደሆነ ጠቅሰው “ የግንባታ ፈቃድና ካርታ እንዲያገኙ እየሰራን እንገኛለን “ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም