ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው

59

ግንቦት 8/2011 ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተከናወኑ የብሔራዊ ደህንነት ስኬታማ ስራዎችን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች ገምግሞ የቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡

በዚሁ መሰረት ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት የቀጣይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸን አፅንኦት በመስጠት የዜጎችን የሰላም ዋስትና የሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ መረባረብ እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፏል።

ለደህንነት ተግዳሮቶች መነሻ ወይም ችግሩን በአጭር ጊዜ እንዳይቀረፍ ከማድረግ አንጻር ዋነኛው ችግር ያለው ከፖለቲካ ስራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጉባኤው መለየቱን  አስታውቋል።

በመሆኑም የደህንነት ስራው ከፖለቲካ ስራው ጎን ለጎን  እንዲሰራና በአንዱ የጎደለው በሌላው እየተሞላ በአጭር ጊዜ አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲከናወን አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከአንዳንድ የአስተዳደር ወሰኖች ጋርም በተያያዘ ሲስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች ያሳዩ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ጋር፣ ክልሎች  ከፌዴራል መንግስት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ሃይሎች ቅኝትና አወቃቀርን በሚመለከት የሚስተዋሉ ችግሮች በህገ መንግስቱ መሰረት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ለማድረግ የሚያስችል ስራ እንዲሰራ ኮሚቴው ወስኗል።

የጸጥታ ኃይሎች ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ የዜጎች በሰላም የመኖር፣  የመንቀሳቀስና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በየደረጃው ያሉ አመራሮችም ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የየአካባቢያቸውን ሰላም  ለማስከበር እንዲሰሩ ያሳሰበው ኮሚቴው ሰላም ወዳዱ ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በንቃት እንዲረባረብ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት  ሁለንተናዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስምሮበታል፡፡

ኮሚቴው የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ እስካሁን የተከናወኑ ስራዎችን  የተመለከተ ሲሆን ለአብነትም በውጭ አገራት የነበሩ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሃገር እንዲገቡ መደረጉ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረው ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ግንኙነት መስተካከሉ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን ገምግሟል፡፡

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች መካሄድ መጀመራቸው፤ የደህንነት ተቋም አመራሮች ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ የሚያስችል የአመራር ለውጥ መደረጉን በጠንካራ ጎን መገምገሙን ነው ያስታወቀው።

ኮሚቴው በዚሁ ወቅት ባለፈው አንድ ዓመት የመከላከያ ሰራዊት ጠንካራ ሪፎርም ካደረጉ ግንባር ቀደም ተቋማት አንዱ እንደሆነና ከአደረጃጀቱ ጀምሮ አጠቃላይ መዋቅሩን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንም አይቷል፡፡ 

በዚሁ ወቅት በአጠቃላይ በጸጥታው ዘርፍ ጠንካራ ስራዎች ቢከናወኑም በርካታ  ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸውም ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

ከነዚሁ ተግዳሮቶች መካከልም በዋናነት ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወይም ደቦዎች፤ ከህገ ወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር እንዲሁም ከማህበራዊ ሚድያ ሀሰተኛ ዜናዎች ተጽዕኖ ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የደህነንት ስጋት ምክንያት መሆናቸውንም አስምሮበታል፡፡

ኮሚቴው የደህንነት ስጋት ምንጮችን በዝርዝር በመለየት ተግዳሮቶቹን በአጭር ጊዜ  በመፍታት የተሟላ ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ዝርዝር ተግባራት ላይ ተወያይቶ የአፈጻጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የመግለጫውን ዝርዝር ይመልከቱ

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተከናወኑ የብሔራዊ ደህንነት ስኬታማ ስራዎችን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች የገመገመ ሲሆን የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡

ኮሚቴው የሀገራችንን ብሔራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎችን በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን ለአብነትም በውጭ ሀገራት የነበሩ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የነበረው ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ግንኙነት መስተካከሉ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን ግምግሟል፡፡

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች መካሄድ መጀመራቸው፤ የደህንነት ተቋም አመራሮች ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ የሚያስችል የአመራር ለውጥ መደረጉን በጠንካራ ጎን የገመገመው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመከላከያ ሰራዊት ባለፈው አንድ ዓመት ጠንካራ ሪፎርም ካደረጉ ግንባር ቀደም ተቋማት አንዱ እንደሆነና ከአደረጃጀቱ ጀምሮ አጠቃላይ የመከላከያ መዋቅሩን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንም አይቷል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በአጠቃላይ በጸጥታው ዘርፍ ጠንካራ ስራዎች ቢከናወኑም በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸው ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

ተግዳሮቶቹ በዋናነት ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወይም ደቦዎች፤ ከህገ-ወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር እንዲሁም ከማህበራዊ ሚድያ ሀሰተኛ ዜናዎች ተጽዕኖ ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የደህነንት ስጋት ምክንያት መሆናቸውንም አስምሮበታል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በጥልቀት ከተወያየ በኃላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በዚህም ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥናና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸን አፅንኦት በመስጠት የዜጎችን የሰላም ዋስትና የሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ መረባረብ እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፏል።

ለደህንነት ተግዳሮቶች መነሻ ወይም ችግሩን በአጭር ጊዜ እንዳይቀረፍ ከማድረግ አንጻር ዋነኛው ችግር ያለው ከፖለቲካ ስራ ጋር የተተያያዘ እንደሆነ በመለየት የደህንነት ስራው ከፖለቲካ ስራው ጋር ጎን ለጎን ተያይዞ እንዲሰራና በአንዱ የጎደለው በሌላው እየተሞላ አስተማማኝ ሰላም በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲከናወን አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከአንዳንድ የአስተዳደር ወሰኖች ጋር በተያያዘ ሲስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች ያሳዩ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ክልሎች ከክልሎች እና ክልሎች ከፌደራል መንግስት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ሃይሎች ቅኝትና አወቃቀር በሚመለከት የሚስተዋሉ ችግሮች በህገ መንግስቱ መሰረት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ለማድረግ የሚያስችል ስራ እንዲሰራ ኮሚቴው ወስኗል።

የጸጥታ ኃይሎች ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ የዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የየአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር እንዲሰሩ ያሳሰበው ኮሚቴው፤ ሰላም ወዳዱ ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በንቃት እንዲረባረብ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ሁለንተናዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስምሮበታል፡፡

ኮሚቴው የደህንነት ስጋት ምንጮችን በዝርዝር በመለየት ተግዳሮቶቹን በአጭር ጊዜ በመፍታት የተሟላ ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ዝርዝር ተግባራት ላይ ተወያይቶ የአፈጻጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም