የሬዲዮ ስርጭት መጀመሩ መረጃን በቀላሉ ለመስጠትና ለመቀበል ይጠቅመናል--የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች

82

ግንቦት 8/2011 የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ ቢ ኤን) በአካባቢያቸው የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት መጀመሩ መረጃን በቀላሉ ለማግኘትና ለመስጠት እንዳሚያስችላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በበኩሉ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭትና ዘመናዊ የስቱዲዮ ግንባታ ሥራ በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት አገልግሎት መጀመሩ ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃን በትኩሱ ለማግኘት ያስችላቸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ድሪቡ ነጋሳ እንዳሉት ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው ከተወሰኑ የሬዲዮ ጣቢያዎች ውጪ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ስርጭት በአካባቢው ይደርስ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡

የስርጭቱ መጀመርና በአካባቢያቸው ተደራሽ መሆን መረጃ በቀላሉ ለመስጠትም ሆነ ለማግኘት ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው በተለይ እየተሸረሸረ የመጣውን የማህበረሰቡን ነባር ዕሴቶች ለማጎልበትና ለአካባቢው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መጎልበት የሚጫወተው ሚና የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በከተማዋ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አህመድ ሙስጠፋ ናቸው፡፡

በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ የኢንጂነሪንግ ዘርፍ አስተባባሪና የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጅማ ቱሉ በበኩላቸው “ኦ ቢ ኤን የመረጃ ፍሰትን በማቀላጠፍ ለሀገር ግንባታ የበኩሉን ሚና እየተወጠ ነው” ብለዋል፡፡

ድርጅቱ መረጃን በአግባቡና በጥራት አድማጭ ተመልካቹ ጋር ተደራሽ ለማድረግ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች ለኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት አገልግሎት የሚውል መሰረተ ልማትና ዘመናዊ የእስቱዲዮ ግንባታ ሥራ በማካሄድ ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

“በባሌ ሮቤ ሰሞኑን የሙከራ ስርጭቱን የጀመረው አዲሱ 96 ነጥብ 5 የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያም የአካባቢውን ማህበረሰብ የመረጃ ፍላጎትን ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ ህዝቡ በልማት ላይ በንቃት እንዲሰተፍ ለማነሳሳት ይረዳል” ብለዋል፡፡

የሬዲዮ ጣቢያው ስርጭት በዞኑ የሮቤና ጎባ ከተሞችን ጨምሮ ከሮቤ በ100 ኪሎ ሜትር ሬዲያስ ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በአሁኑ ወቅት በሬዲዮ የስርጭት ዘርፍ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 70 በመቶ ሽፋን እንዳለው የተናሩት አቶ ጅማ፣ በግንባታ ላይ የሚገኙት ሲጠናቀቁና በነባሮች ላይ የማሻሻያ ስራ ሲጠናቀቅ ሽፋኑን ወደ 75 በመቶ እንደሚያድግ አመልክተዋል።

“ ባሌ ሮቤ ኤፍ ኤም 96 ነጥብ 5” የሚል ስያሜ የተሰጠው የሬዲዮ ጣቢያ ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ድረስ “ ከግንቦት 3 ቀን 2011 ጀምሮ አዳማ ከሚገኘው የድርጅቱ ዋና ስቱዲዮ ጋር በመገናኘት በአፋን ኦሮሞ የሙከራ ስርጭት ሥራውን መጀመሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም