ውህደቱ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሳሌ ነው-የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎች

88

ግንቦት 8/2011  በቅርቡ ተዋህደው ስያሜያቸውን ወደ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀየሩ አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደታቸው ለሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምሳሌ መሆኑን አጋር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።

በቅርቡ አምስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት(ኦህዲኀ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት(ሽግግር)፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት(ቱሳ)፣ ኢትዮጵያችን ህዝባዊ ንቅናቄ(ኢትዮጵያችን) እና ደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ቅንጅት(አረንጓዴ ኮከቦች) ተዋህደውኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰኘ አንድ ፓርቲ ማቋቋማቸው ይታወሳል።

በዚህም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውህደት ለሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ምሳሌ የሚሆንና በአሪገሪቷ እየተከናወነ ያለውን ለውጥ የሚያግዝ ነው ሲሉ የፓርቲው አጋር ፓርቲዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም ተመሳሳይ ዓላማን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን በቅንጅት እንዲሰሩና ጠንካራ ሃሳብና ፖለቲካን እንዲያራምዱ እድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

አዲሱ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር በቀጣይ የፓርቲው አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ጉባኤ እያካሄደ ሲሆን ዛሬ የፓርቲውን ሊቀመንበር የሚመርጥና ተመራጩም ቃለ መሃላ የሚፈጽም ይሆናል።

በጉባኤው የተገኙት ሌሎች አጋር የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በፓርቲው ውህደት ላይ ያላቸውን አስተያየትና መልካም ምኞት ገልጸዋል።

የኢህአዴግ ተወካይ አቶ አክሊሉ ታደሰ አገሪቷ ባለፈው አንድ አመት ካደረገቻቸው ለውጦች መካከል የፖለቲካ ሪፎርሙ አንዱና ዋነኛው ነው ይላሉ።

በዚህም ኢህአዴግና የኢፌድሪ መንግስት ሪፎርሙን ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ በውጭና በሃገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ትግላቸውን በአገራቸው ሆነው እንዲያጠናክሩ ድጋፍና እገዛ ከማድረግ ባሻገር ጠንካራና ጽኑ አቋም ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ መፈጠር እንዳለበት ያምናል ብለዋል።

አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድ አቋም መምጣታቸው ጠንካራ ሃሳብ እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታን የፈጠረና ተስፋ የሚጣልባቸው እንዲሆኑ ከማስቻሉም ባሻገር ለሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ምሳሌ ይሆናል ነው ያሉት።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው በአገሪቷ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ በተለይም ሰላም፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በተቀናጀ መንገድ ለመታገል አምስቱ ድርጅቶች የነበራችሁን ልዩነት በማስቀረት መዋሃዳችሁ ለቀጣዩ የትግል ጉዞ አንድ ምእራፍ ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ይህም ለሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች ምሳሌ የሚሆንና በማንኛውም የአገሪቷ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመስራት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እድል የሚፈጥርላቸው እንደሆነና በማንኛውም የአገሪቷ የጋራ ጉዳዮች ላይ ኦነግ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር በአብሮነት ለመስራት ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።

በቀጣይም ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሻለ ይዘት ያለው የፖለቲካ አቋም የሚያሳይበትና በአሁኑ ወቅት የዜጎች ጥያቄዎችን ለመመስ የሚያስችል ስርዓት እንደሚገነባ እምነታቸው መሆኑን አክለዋል።

የአፋር ህዝብ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ሃላፊና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም አሁንም በአገሪቷ የሚስተዋለውን የዜጎች መፈናቀል፣ የሰላም እጦትና መሰል ችግሮችን ለማስቀረት ፓርቲዎች በቅንጅት የመታገል ልምድ ማዳበራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

በተለይም የግል ሃሳብን በማሸነፍ፣ ለህዝቡና ለአገር ቅድሚያ የመስጠትና ዘመናዊ የፖለቲካ ስርአትን ለማራመድ "ቁጥሩ የበዛ የፖለቲካ ድርጅት ፋይዳ የለውም" ያሉት ሊቀመንበሩ ህዝቡንም ውዥንብር ውስጥ ከማስገባት መጠነኛ ቁጥር ያለው ፓርቲ የመፍጠር ሃላፊነት የሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቤት ስራ ሊሆን እንሚገባም አስገንዝበዋል።  

ለዚህም ደግሞ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይህንን በጋራ የመስራት ጅማሬን ተዋህዶ ያሳየ በመሆኑ ጠንካራ ድርጅት እንደሚወጣው አምነታቸው መሆኑን ገልጸው፤ ሌሎች መሰል ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይህንን እንዲጋሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ አምስቱ ፓርቲዎች ወደ አንድ ጠንካራ ድርጅት መምጣታቸው የተሻለ የፖለቲካ ሃሳብ እንዲያራምዱ እድል የሚፈጥርና ለሌሎች ፓርቲዎችም መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ይላሉ።

በተጨማሪም በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ፓርቲያቸው በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክታቸውንም አሰተላልፈዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ተወካይ አቶ በለጠ ካሳ እንዲሁ ፓርቲዎችን አክስሞ ወደ አንድ የተሻለ ድርጅት የመምጣት ልምድ ያልተለመደ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ልምድ ማስጀመርና ወደ ሌሎች ድርጅቶች ለማስረጽ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያሳየው ቁርጠኛ አቋም ለሌሎቸ ድርጅቶችም አርአያ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

በዚህም ፓርቲያቸው አብን በማንኛውም ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጥምረት የመስራት ፍላጎቱ ይበልጥ እንዲነሳሳና እንዲዳብር ያደረገ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሁሉም አጋር ተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ለኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንለትም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዲስ ሊቀመንበር ሹመትና በጉባኤው የተገኙ ግብዓቶችና የቃል ኪዳን ስምምነትን በሚመለከት  ከሰአታት በኋላ ዝርዝር መረጃዎቹ ይፋ ይሆናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም