‘’አካቻ ለምለም‘’ የተባለውን የግራር ዝርያ ለእንሳሳት ምግብነት ለማዋል የተካሄደው ምርምር ውጤታማ መሆኑ ተጠቆመ

152

   ግንቦት 8/2011 ‘’አካቻ ለምለም‘’ በመባል የሚታወቀው የግራር ዝርያን ለእንስሳት ምግብነት ለማዋል የተካሄደው ምርምር ውጤታማ መሆኑን የትግራይ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በተክሉ ላይ በተካሄዱ የምርምር ሥራዎችና በተገኘው ውጤት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል።

የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አባዲ ግርማይ እንደገለጹት የግራር ዛፍ ዝሪያው ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባለፈ ለእንስሳት ቀለብ እንዲውል ለአምስት ዓመት የተካሄደው የምርምር ሥራ ውጤት ተገኝቶበታል። 

በእዚህም ተክሉ ለቤት እንስሳት፣ ለዶሮ እና ለንቦች መኖነት ጠቃሚ መሆኑን በጥናቱ መረጋገጡን ነው የገለጹት።

በተክሉ ምርምር ላይ የተሻለ ተሞክሮ ወዳላት ሴኔጋል የተክሉን ዘር በመላክ ለሰው ምግብነት መዋል የሚችልበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ምርምር እየተካሄደ መሆኑንም ዶክተር አባዲ ተናግረዋል።

የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ ከኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ቀጣይ ምርምር ለማካሄድ እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል። 

የትግራይ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ሀብት ምርምር ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ክንፈ መዝገበ በበኩላቸው የምርምር ስራው በክልሉ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች መካሄዱን ገልጸዋል።

በምርምሩ የተክሉን ቅጠል ከሌሎች የእንስሳት መኖዎች ጋር በመቀላቀል እንስሳት እንዲመገቧቸው መደረጉንንና በእዚህም በክብደትና በውፍረት የተሻለ ሆነው መገኘታቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የተክሉን ፍሬ በመፍጨትና ከሌሎች ጥራጥሬዎች ጋር በመቀላቀል ለዶሮዎች መኖ እንዲውል በተደረገው ጥረት ዶሮዎቹ በእንቁላልና በሥጋ የተሻሉ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

የአካቻ ተከል በዓመት ሁለት ጊዜ አበባ የሚያወጣ በመሆኑ ለንቦች ቀለብ ተመራጭ እንደሚያደርገውና በበጋ ወቅትም ቅጠሉ ስለማይረግፍ ቀጣይነት ላለው የእንስሳት ቀለብ ተመራጭ መሆኑን በምርምሩ ላይ መረጋገጡን አመልክተዋል።

ተመራማሪው እንዳሉት ከተክሉ አበባ ከሚቀስሙ ንቦች የሚገኘው ማር በጣዕሙም ሆነ በመልኩ ሌሎች ተክሎች ከሚቀስሙ ንቦች ከሚገኘው ማር የተለየ አለመሆኑን በምርምር ታውቋል።

” ከዚህ ቀደም የአካቻ ተክል የሚቀስሙ ንቦች እንደሚጎዱ፣ የማሩ ጣዕምና መልክም እንደሚቀየር በህብረተሰቡ ላይ የነበረውን የተሳሰተ ግንዛቤ ስህተት መሆኑንም በምርምር ስራው ተረጋግጧል” ብለዋል።

ምርምሩ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ከወርልድ ቪዥንና በአውስትራሊያ ከሚገኝ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር መካሄዱንም ገልጸዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን አፅቢ ወንበርታ ወረዳ ነዋሪና የምርምሩ ተሳታፊ ሴት አርሶ አደር አብርሃት መሀሪ በበኩላቸው የአካቻ ተክልን ተክለው ቅጠሉን ለበጎች ቀለብ በማዋል የተሻለ ውፍረት ያላቸው በጎት ማርባት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የአካቻ ተክልን በመመገብ ያሳደጓቸውን በጎች ከሌሎች በጎች እስከ 800 ብር ብልጫ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣዩ ክረምት ተክሉን በማስፋትና ፍሬውን ለዶሮዎች ቀለብ ለማዋል መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተብሎ ከ40 ዓመታት በፊት ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮዽያ እንደገባ የሚነገርለት የአካቻ ተክል ድርቅን የመቋቋም አቅም እንዳለውና ከሌሎች ተክሎች ጋር ተስማሚ መሆኑን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ ተመራማሪዎች፣ በምርምር ሥራ ላይ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ  አካላት ተሳትፈዋል ።