የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር ሹመትን አፀደቀ

100

አዲስ አበባ  ግቦት 8/2011 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር እንዲሁም የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢን ሹመት  አፀደቀ።

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው የ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 39ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበለትን ሹመት መርምሮ አጽድቋል።

በዚህም ዶክተር ጣሰው ገብሬ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ደግሞ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው በ25 ተቃውሞና በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራራያ ተሰጥቶበታል።

በዚህም የኮሚሽኑን መቋቋም የተቃወሙ የምክር ቤቱ አባላት እንዳሉት የኮሚሽኑ መቋቋም በራሱ ህገ-መንግስቱን የሚጻረር በመሆኑ  እንደማያምኑበት ተናግረዋል።

አባላቱ አክለውም ከፍትሃዊነትና ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት አንጻር ህገ መንግስቱ ያለውን ሃላፊነት የሚጋፋ መሆኑን አንስተዋል።

የኮሚሽኑ መቋቋም ህገ መንግስቱን እንደማይጻረርና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኮሚሽኑን ለማቋቋም የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት አድርጎበት በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ ሹመትንም አጽድቋል።

በዚህ መሰረት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌልን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፤ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ደግሞ ምክትል የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው በአራት ተቃውሞና በአስር ድምጸ ተአቅቦ ሹመታቸው ጸድቋል።

በሹመቱም ወቅት ከምክር ቤት አባላት የህጋዊነትና የአካሄደ ተጥሷል አስተያየት ተነስቷል።

በዚህም የኮሚሽኑ አመራሮች ሹመታቸው በምክር ቤት ሳይጸደቅ ወደ ስራ መግባታቸው ትክክል እንዳልሆነና ከአመለካካትና ከተግባር ጋር ተያይዞ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ያለቸውን ብቃት አስመልክቶም ጥያቄ  ተነስቶ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሹመት የቀረቡ የኮሚሽኑ አባላት በምክር ቤቱ ሳይሾሙ ቢሮ ከፍተው ወደ ስራ እንዳልገቡና ይህ የህጋዊነት ጥያቄ የማያስነሳ መሆኑም ምላሽ ተሰጥቶበታል።

ተሿሚዎቹም በህግ ልምዳቸውም የአጠቃላይ አገራዊ ሁኔታዎችንና ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ብቃት እንዳለቸው የታመነበት መሆኑ ተነግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም