የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቅ ለችግር እንዳጋለጣቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

59

ግንቦት 8 ቀን 2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ግንባታቸው የተጀመሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ከነዋሪዎቹ መካከል በሐሮ ሊሙ ወረዳ የደንጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መንግስቱ ዴሬሳ እንዳሉት የበሪሶ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በ2006 ዓ.ም ቢጀመርም ባልታወቀ ምክንያት ተቋርጧል።

"በእዚህም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ንጽህናው ያልተጠበቀ ወራጅ የወንዝ ውሃ ለመጠቀምና ለውሃ ወለድ በሽታዎች እየተጋለጥን ነው" ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጀማነሽ ሞሲሳ በበኩላቸው ርቀት ሄደው የሚቀዱት ውሃ ንጽህናው የጎደለው በመሆኑ በተለይ ሕፃናት ለውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋልጠው በየጊዜው ወደ ጤና ተቋማት እንደሚመላለሱ ተናግረዋል፡፡


የበሪሶ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ አመላ ደበሎ በበኩላቸው በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት በመኖሩ ለሥራቸው እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ለጤና አገልግሎት ውሃ ለማግኘት ረጅም መንገድ ተጉዘው የሚያመጡት ውሃ ንጽህናው ያልተጠበቀ ከመሆኑም በላይ 20 ሊትር ለሚይዝ አንድ ጀሪካን ውሃ በ12 ብር እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል፡፡


ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በጤና ጣቢያው እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አመላ በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎችን በአካባቢው ለማቆየት አለመቻሉን አመልክተዋል፡፡


በሲቡ ስሬ ወረዳ ለሊሳ ቀበሌ ግንባታው በ2006 ዓ.ም የተጀመረው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በወቅቱ አለመጠናቀቅ የአካባቢውን ሕዝብ ለንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር መዳረጉን የተናገሩት የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ምሥጋኑ ዋቅሹም ናቸው፡፡


የዞኑ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጄ አበራ በበኩላቸው በዞኑ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ከ21 ሚሊዮን 971 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ በየዓመቱ ግንባታቸው የተጀመሩ 39 የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው በሕዝብ ላይ ቅሬታ መፈጠሩን አስረድተዋል።


በዞኑ ግንባታቸው ለተጀመሩ አብዛኞቹ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ የኦሮሚያ ውሃ ሀብት ልማትና ኢነርጂ  ቢሮ በጨረታ ሥራውን ቢወስድም ቁሳቁሶችን በወቅቱ ማቅረብ እንዳልቻለ ተናግረዋል።

የቁሳስ በወቅቱ አለመቅረብ ሥራ ተቋራጮቹ ሥራውን አቋርጠው እንዲወጡ ምክንያት መሆኑንና ግንባታቸው እስከ ዛሬ ድረስ መጓተቱንም አቶ ደረጄ አስረድተዋል፡፡


ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች አስፈላጊውን ክትትል ከማድረግ ይልቀ ቸልተኝነት ማሳየታቸው በዞኑ ለንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ከፍተኛ ወድቀት ማስከተሉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡


ግንባታቸው ወደ መጠናቀቅ ደረጃ ለደረሱና የሚያስፈልጋቸው ቁሳቁስ በአካባቢውና በአዲስ አበባ ሊገኙ የሚችሉትን ፕሮጀክቶች የዞንና የወረዳ ባለሙያዎችን በመጠቀም ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ ከነቀምቴ ከተማ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የክሬን፣ የመሳሪያና የባለሙያ ትብብር በመጠየቅ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡


በሌላ በኩል የሲቪል ሥራቸው ተጠናቆ ግንባታቸው የተቋረጡ የውሃ ፕሮጀክቶች በወርልድ ቪዥን እና በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ እንዲጠናቀቁ ለተቋማቱ ጥያቄ ቀርቦ አዎንታዊ ምላሽ ማሳየታቸውን ነው የገለጹት።


የኦሮሚያ ውሃ ሀብት ልማትና ኢነርጂ ቢሮ የኮንትራት አስተዳደርና የኮንስትራክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጉርሜሳ ኦልጅራ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ግንባታቸው በ2004፣ 2005 እና 2006 ዓ.ም የተጀመሩ የውሃ ፕሮጀክቶች መቋረጣቸውን አምነዋል። 

ግንባታ ግብአቶችን በወቅቱ ከውጭ አገር ገዝቶ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንቅፋት መሆኑን አስረድተው በአሁኑ ወቅት ግዥውን ወደ አገር ውስጥ በመመለስ ብዙዎቹን ዕቃዎች ለመግዛት መቻሉን ጠቁመዋል።


በቀጣይ ስራውን በኢንተርፕራይዝ ለተደረጁ የዞኑ ወጣቶች በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም