በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሕዝብ ጥያቄዎችን አልመለሱም የተባሉ 272 አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነሱ

54
ሐረር ግንቦት 29/2010 የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሕዝብ ጥያቄዎችን አልመለሱም ያላቸውን 272 አመራሮች ከኃላፊነት ማንሳቱን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ እንደገለጹት ከኃላፊነት የተነሱት የአመራር አካላት በዞንና በወረዳ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። የአመራር አካላቱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በዞኑ ለ20 ቀናት በተካሄደ የተሀሃድሶ ግምገማ መሰረት ሂስና ግለ ሂስ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ብበቃት አለመወጣታቸውን ከስምምነት በመድረሱ መሆኑን ተናግረዋል። በተሃድሶ ግምገማው የአመራር አካላቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን አለመመለስ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ውስጥ መዘፈቅ፣ በፕሮጀክት ግንባታ ሥራዎች የአፈጻጸም ጉድለት ማሳየት፣ እንዲሁም የህግ የበላይነትን አለማስከበርን ጨምሮ በሌሎች የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሥራዎች ላይ ድክመት ማሳየታቸውን አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል። አስተዳዳሪው እንዳሉት የግምገማ ሂደቱን ከዞን እስከ ወረዳና ቀበሌ  ድረስ በማውረድ ህዝቡ እንዲወያይበትና ሀሳብ እንዲሰጥበት የተደረገ ሲሆን የአመራሮችን ብቃትና ጥንካሬን የመለየት ስራም ተከናውኗል። በግምገማው ሂደት በተደረገው መተማመን ለሕብረተሰቡ የልማትና፣ የመልካም አስተዳደርና መሰል ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ አለመስተጣቸው የተረጋገጡ 272 አመራሮችን ከኃላፊነት በማንሳት በምትካቸው ሌሎች መሾማቸውን አስረድተዋል። በአዲስ ከተሾሙት አመራሮች መካከል 261ዱ በዞኑ ባሉ 24 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር በአመራርነት የሚሰሩ ሲሆን ቀሪዎቹ 11 በዞን ደረጃ  የተሾሙ መሆናቸው አመልክተዋል። ኦህዴድ የህዝቡን የልማት ጥያቄ በሚገባ በመረዳት ጥንካሬዎቹን ለማስቀጠልና ደካማ ጎኖቹን ለማረም እንደሚሰራ ገልጸዋል። ከልማቱ ጋር እኩል እያደገ የመጣውን የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድም ድርጅቱ የጀመረውን የአሰራር ስርዓት ለውጥ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ድርጅቱ ያደረገው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ መልካም መሆኑን የገለጹት የሐረማያ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብዲ ኢብራሂም በበኩላቸው "እንደዚህ ዓይነት ስር ነቀል ለውጥ ሲደረግ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፤ ይህ ደግሞ ለህብረተሰቡ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለው" ብለዋል። አዳዲስ የተሾሙትም ሆኑ ነባሩ አመራሮች የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። በአሁኑ ወቅት አመራሩ በልማት፣ በሰላምና በጸጥታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ያለችው  ወጣት ፈሪያ አሊ በበኩሏ ሕብረተሰቡ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ከተሿሚዎቹ ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበት አመልክታለች።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም