የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ ፋይናስ ስርዓት ተደራሽነት የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል-ንግስት ማክሲማ

215

ግንቦት 7 /2011 ኢትዮጵያ ተደራሽ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት ለምታከናውነው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ እንደማይለያት የኔዘርላንዷ ንግስት ማኪሲማ ተናገሩ። 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ  የአካታች ፋይናንስ ልማት አምባሳደር  ንግስት ማክሲማ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያካሄዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ንግስቲቷን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ንግስት ማክሲማ በዚህን ወቅት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለፋይናስ  ተደራሽነት  ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ስለጉዳዩም ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

   ጠቅላይ ሚንስትሩ በርካታ የለውጥ አጀንዳዎች እንዳሏቸው እንደተገነዘቡ በመጠቆም።

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ዲጂታል መታወቂያ ሙከራ እየተከናወነ መሆኑን እንደተገነዘቡም ጠቁመዋል።

ይህን አሰራር አገር አቀፋዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት  እርሳቸውና አጋሮቻቸው በሚደግፉበት ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ንግስት ማክሲማ አውስተዋል።

 የፋይናንስ ስርዓትን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪም በረዥም ጊዜ እቅድ የገጠሩ ማህበረሰብ  የጤናና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ዙሪያም ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በኢኮኖሚው ዘርፍ የግል በለሃብቶችን ተሳታፊ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ ተግባራትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን ገልጸዋል

በቴሌኮሙኒኬሽን ላይ የተሰራውን ለአብነት በመጥቀስ።

ንግስት ማክሲማ ትውልዷና እድገቷ አርጀንቲና ሲሆን ከኔዜርላንዱ ንጉሳዊ ቤተሰብ የተቀላቀሉት እ.አ.አ በ2001 የኔዘርላንድ ዜግነት ካገኙ በኋላ ሆኖ ከኔዘርላንዱ ንጉስ ዊለን አለክሳንደር ጋር በጋብቻ በመተሳሰር መሆኑ ይታወቃል።

ንግስት ማክሲማ እ.አ.አ በ2013 የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ወክለው በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።