ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኡጋንዳ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ

82
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰኔ 1 እና 2 ቀን 2010 ዓ.ም በኡጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን የሚያካሂዱት በፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ግብዣ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።መሪዎቹ በሁለትዮሽ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተጠቁሟል። ዶክተር አብይ በዩጋንዳ የሚያደርጉት ጉብኝት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረውን የሁለቱን አገሮች ወዳጅነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በኢጋድ ጥላ ስር በደቡብ ሱዳን ሠላም ሂደትና በሶማሊያ ፀጥታ ላይ ተባብረው እየሰሩ እንደሚገኙና ሁለቱ አገሮች የሶማሌያውያንን ሰላም ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው አሚሶም የመከላከያ ሃይል ማሰማራታቸውን መግለጫው አብራርቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የኡጋንዳ ብሄራዊ የጀግኖች በዓል ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዶክተር አብይ ከዚህ በፊት በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት በማድረግ የሁለትዮሽና አካባቢያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም