ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የኔዘርላንድስ ንግስት ማክስማን ተቀብለው አነጋገሩ

152

ግንቦት 7 /2011ዓምአካታች የፋይናንስ ስርዓትን እውን ማድረግ በሌሎችም ዘርፎች ላይ የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። 

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉትን የኔዘርላንድስ ንግስት ማክስማን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ንግስት ማክሲማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካታች ፋይናንስ ልማት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።  

ወደኢትዮጵያ የመጡትም በዚህ ዙሪያ በኢትዮጵያ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ ለማየት ነው።

የገጠርና ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ የባንክ አገልግሎቶችን፣ ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን፣ ኤሌክትሮኒክ ንግድን እና ሌሎች ዘመናዊ የፋይናንስ ክፍያና የመገበያያ መስተጋብሮች አካታች የፋይናንስ ስርዓትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ስልቶች ተደርገው ይወሰዳሉ።

ይህም ዜጎችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባሻገር ብሄራዊ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ የተቀላጠፈና ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ይታመንበታል።

ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር ከመነጋገራቸው ቀደም ብሎም ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መክረዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅም ከንግስቲቱ ጋር ሲወያዩ የገለፁት አካታች የፋይናንስ ስርዐትን እውን  ማድረግ በሌሎችም ዘርፎች ላይ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ነው፡፡

አካታች የሆነ የፋይናንስ ስርዐት እንዲጎለብት የኔዘላንድሷ ንግስት ለሚያደርጉት ጥረት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ምስጋና አቅርበዋል።

ንግስት ማክስኢማን በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማጎልበት የምታከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር መወያየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ውጤታማ የሆነ አካታች የፋይናንስ ስርዐት ለመዘርጋት የሚደረገው ጥረት በተለይም ሴቶችን ማቀፍ እንዳለበትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በመለየት መሰራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡