የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለአገር ልማት ፣ ብልጽግናና ሰላም ግንባታ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለባቸው

106

ግንቦት 7/2011 የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለአገር ልማት፣ ብልጽግናና ሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ማጎልበት እንደሚገባቸው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አሳሰበ።

በባህል ቱሪዝም፣ አካባቢና ቅርስ ጥበቃ፣ የህትመት ጋዜጠኝነትና ዶክመንተሪ ፊልም ዙሪያ በቻይና  በተካሄዱ ጉባኤዎች 50 ኢትዮጵያዊያን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በዚህም ለ21 ቀናት ቆይታ የነበራቸው ሰዎችም ለሌሎች የአገር ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ ዛሬ አድርገዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኪነ-ጥበብ አስተሳሰብን በማስፋት፣ በማዘመንና ተጽእኖ በማሳደር ረገድ ጉልህ ሚና አለው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የዘርፈ ብዙ የስነ-ጥበብና ኪነ-ጥበብ ታሪክ ባለቤት እንደመሆኗ በዘርፉ የሚገኙ ሙያተኞች በጥበባዊ ሙያቸው አቅማቸውን እየገነቡ ዜጎችን በስነ ምግባር በማነጽና በማስተማር ሙያዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ዘርፉ ባደገ ቁጥርም በባህሉ፣ በማንነቱና በስነ-ምግባሩ የሚኮራና ለአገሩ ሰላም የሚተጋ ጠንካራ ዜጋ መፍጠር ይቻላል ተብሏል።

በተለይም በባህል ኢንዱስትሪው በስዕልና ቅርጻ ቅርጽ፣ በሙዚቃ፣ በተውኔት፣ በፊልም፣ በዕደ ጥበብና በስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ስራዎች ወጣቱ ትውልድ የራሱን ባህልና ታሪክ እንዲያውቅ በማድረግ ረገድም ትልቅ ስራ መስራት እንዳለባቸውም ነው የተገለጸው።

በዚህም ሙያተኞች የተለያዩ ኪነጥበባዊና ማህበራዊ ስራዎችን በመስራት በህብረተሰቡ ውስጥ ለእድገት የሚረዳ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው ቻይና ማንነትንና ነባር እውቀቶችን አጣምሮ አገራዊ እድገትን ማስመዝገብ እንደሚቻል ተምሳሌት የምትሆን አገር መሆኗን ይገልጻሉ።

በዚህም በምልከታቸው መሰረት በጥበብ ስራዎቻቸው ውስጥ ለመግለጽ፣ አዳዲስ ስራዎችና እውቀቶችን ለሌሎች ለማካፈልና በአገሪቱ ኪነ-ጥበብ ዘርፍ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ፍላጎት እንዳደረባቸውም ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ የጥበብ ሰዎችም እንደዚህ ያሉ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ፣ አዲስ አሰራርና እውቀት እንዲቀስሙ ማድረግ ለአጠቃላይ አገራዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ቻይናውያን  ስነ-ጽሁፎቻቸው፣ ስነ-ስዕሎቻቸውና ትወናቸው ባጠቃላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶቻቸው 53 ደርሰዋል።

በእነዚህም ጥበቦቻቸው እስከ ዘመናዊ ሲኒማና ሙዚቃዊ ትያትሮቻቸው ድረስ በዓለም የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ከጣልያንና ከስፔን በመቀጠል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም