በኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ አገልግሎትና ልማትን ለማጠናከር ለተጀመረው ጥረት ድጋፍ ይደረጋል – የኔዘርላንድስ ንግስት

277

ግንቦት 7/8/2011 በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትንና አካታችነትን ለማጠናከር የአገሪቱ መንግስት ለጀመረው ጥረት አስፈላጊውን የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርጉ የኔዘርላንድስ ንግስት ማክሲማ ገለፁ። 

በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የኔዘርላንድ ንግስት ማክሲማ በኢትዮጵያ የአካታች ፋይናንስ ልማት ያለበትን ደረጃ ለመገንዘብ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ጋር ተወያይተዋል።

ንግስት ማክሲማ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካታች ፋይናንስ ልማት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ በዘርፉ በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ ለማየት ነው ወደዚህ የመጡት።

በርካታ የዓለም አገራት የአካታች ፋይናንስ ልማትን ሳይጠቀሙ ለረጅም ጊዜያት የቆዩ ቢሆንም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ይህ ደግሞ በዘመናዊ የክፍያ መንገዶች ማለትም በኢኮሜርስ፣ ኢ ፔመንት እና ሌሎች ዘመናዊ የፋይናንስ ክፍያ ሥርዓቶችን በመዘርጋት  የአካታች ፋይናንስ ልማት እንዲስፋፋ እያደረገ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ላይ ይገኛል።

በመሆኑም የኔዘርላንድ ንግስት ማክሲማ ይህ የአካታች ፋይናንስ ልማት በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

በዚህ መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲያድግ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት እየተከናወነ ያለውን ሥራ አብራርተዋል።

ለአብነትም የኢ-ኮሜርስ ህግ ከመቅረጽ ጀምሮ፣ የዲጂታል መታወቂያ እና የኢ-ፔመንት ክፍያ ስርዓቶችን ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘርፉ ኔዘርላንድ ያላትን የካበተ አቅምና ልምድ በሰው ሃይል ልማት፣ በእውቀት ሽግግር፣ የባለሙያ እና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

ንግስት ማክሲማ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማጠናከርና የቴሌኮም ዘርፉን ፕራይቬታይዝ ለማድረግ እየተሄደበት ያለውን ርቀት ጠይቀው ምላሽ አግኝተዋል።

ዘርፉን ለመደገፍ እርሳቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የአካታች ፋይናንስ ልማት ልዩ መልዕክተኛ በመሆናቸው  የአካታች ፋይናንስ ልማትን የሚደግፉ የልማት አጋሮችን እንደሚያስተባብሩ ተናግረዋል።

በዚህም በቴክኒክ እና በተባበሩት መንግስታት ማዕቀፍ በአካታች ፋይናንስ ልማት ዘርፍ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በመጨረሻም ለዘርፉ እድገት ማነቆ ሊሆን ይችላል ያሉትን በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ግንኙነት የፍጥነት ዝቅተኝነት እንዲሻሻል ምክረ ሀሳብ መስጠታቸውንም ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ተናግረዋል።

የኔዘርላንድስ ንግስት ማክሲማ ባሳለፍነው ጥር ወር በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተገናኘትው ነበር።

እንዲሁም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው እንደነበረም ይታወሳል።