የአቶ ንጉሴ ደስታ ስርዓት ቀብር ተፈጸመ

46
ማይጨው ግንቦት 29/2010 የደደቢት እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የነበሩት የአቶ ንጉሴ ደስታ ስርዓት ቀብር በማይጨው ከተማ ተፈጸመ፡፡ ሥርአተ ቀብራቸው ዛሬ በማይጨው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተፈጸመው ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የስፖርት አፍቃሪዎች በተገኙበት ነው። የመከላከያና የደደቢት እግር ኳስ ክለቦች አባላትና የሥራ ኃላፊዎች፣ የትግራይ ክልልና የትግራይ ደቡባዊ ዞን ከፍተኛ አመራር አካላትም በአሰልጣኙ የቀብር ሥነስርአት ላይ ተገኝተው ሀዘናቸውን ገልጸዋል። በቀብር ሥርአቱ ላይ የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ አቶ ንጉሴ ደስታ ከእናታቸው ከወይዘሮ መድህን ገብረኢየሱስና ከአባታቸው ከአቶ ደስታ አለም በ1960 ዓ.ም በትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው ከተማ ነው የተወለዱት ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በማይጨው ዘላዓለም ደስታ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ አቶ ንጉሴ በ1976 ዓ.ም በወታደርነት ተቀጥረው መቀሌ ከተማ የነበረውን የ16ኛ ክፍለጦር የእግር ኳስ ቡድንን በመቀላቀል የእግር ኳስ ህይወታቸውን ጀምረዋል፡፡ ከ1977 እስከ 1980 ዓ.ም የትግራይ ክፍለጦር የእግር ኳስ ቡድን አባል በመሆን ሲጫወቱ እንደነበረም የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ የቀድሞ መከላከያ ሚኒስቴር የእግር ኳስ ክለብን ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ በመቀላቀል ለሦስት ዓመት በተጨዋችነት የሰሩ ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላም እስከ 1995 ዓ.ም የባህር ኃይልና የመከላከያ እግር ኳስ ክለቦች ተጫዋች በመሆን አገልግለዋል፡፡ በህይወት ታሪካቸው እንደተመለከተው አቶ ንጉሴ ደስታ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ዓመታት የሀገር መከላከያ የእግር ኳስ ቡድንን በረዳት አሰልጣኝነት፤ ከ2000 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ከ2003 አስከ 2004 ዓ.ም ባለው ግዜ ውስጥም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ አየር ኃይል የእግር ኳስ ቡድኖች ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከ2005 እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ የደደቢት እግር ኳስ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት የጥሎ ማለፍ ፕሪሜየር ሊግ ሻምፒዮን በማድረግ ውጤታማ ተግባር መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡ አቶ ንጉሴ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ የወልዲያን እግር ኳስ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የመሩ ሲሆን በዚህም ክለቡ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሜየር ሊግ እንዲያድግ አድርገዋል፡፡ ዘንድሮም እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ የደደቢት እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ህይወታቸው በድንገት ያለፈው አቶ ንጉሴ ደስታ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበሩ ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም