የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና እንደቀጠለ ነው

62

 አዲስ  አበባ ግንቦት 7 / 2011 ከትናንት በስቲያ በተጀመረው የ2011 ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ክለቦች ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በሁለተኛ ቀን ውሎው በቡድን የዙር ውድድር የተለያዩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡

በታዳጊ ሴቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌትሪክን 3 ለ 2 ኢትዮ ኤሌትሪክ የካ ክፍለ ከተማን 3 ለ 0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቁጥር ሁለትን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

በአዋቂ ወንዶች ኦሮሚያ ፖሊስ ማማስ ኪችንን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌትሪክን 3 ለ 2 አሸንፏል።

እንዲሁም በታዳጊ ወንዶች ኦሮሚያ ፖሊስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 2  ረትቷል።

በኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የዛሬ የሶስተኛ ቀን ውሎ በታዳጊ ወንዶች እና በታዳጊ ሴቶች የግማሽ ፍጻሜ በአዋቂ ወንዶች የማጣሪያ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በታዳጊ ወንዶች ኦሮሚያ ፖሊስ  ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቁጥር ሁለት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ-ኤሌትሪክ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በተጨማሪው በታዳጊ ሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቁጥር አንድ የሚጫወቱ ሲሆን፤ በአዋቂ ወንዶች ማማስ ኪችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር ይጫወታሉ።

በአጠቃላይ በሻምፒዮናው የሚያሸንፈው ክለብ ከሐምሌ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ በሚካሄደው 25ኛው የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍም ከኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ማማስ ኪችን፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እና የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) በሻምፒዮናው ላይ በሁለቱም ጾታዎች እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።

በሻምፒዮናው ላይ 46 ወንድና 34 ሴት በድምሩ 80 ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው።

የ2011 ዓ.ም ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

ከጥር 27 እስከ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ከተማ በተካሄደው የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ አሸናፊ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም