ለባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ተደረገ

92

ባህርዳር  ግንቦት 7 / 2011 የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብን ለማጠናከር የሚያግዝ   የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ተደረገ።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ አማረ ዓለሙ  ትናንት በሰጡት መግለጫ ክለቡ እስካሁን ከሜዳና ከክለቡ ደጋፊ አባላት ከሚያገኘው ገቢ ሌላ ወጪውን እየሸፈነ ያለው  የከተማ አስተዳደሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ክለቡ በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያን ፒሪሜር ሊግ በመቀላቀል እስካሁን ባደረጋቸው ውድድሮችም አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በቀጣይ ክለቡ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆን እንዲችል መደገፍ የሚፈልጉ አካላት በቀላሉ የሚያግዙበት አዲስ የኤስ ኤም ኤስ የገቢ ማሰባሰቢያ ቁጥሮችን ይፋ አድርጓል።

6753 እና 6754 ይፋ የተደረጉት የገቢ ማሰባሰቢያ ቁጥሮች ሲሆኑ ይህም  የሚሰራው ከትናንት ጀምሮ ኤፕላስ ከተሰኘ የግል ድርጅትና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ነው።

ክለቡን መርዳት የሚፈልጉ ወገኖች 6753 ብለው በመላክ ከአምስት ብር ጀምረው የፈለጉትን ያህል ብር መርዳት እንደሚችሉ ተገልጿል።

ደጋፊ አባል መሆን የሚፈልጉ ወገኖች ደግሞ 6754 ብለው ብለው በመላክ ተመዝግበው በሳምንት አንድ ብር ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።

የባህርዳር እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ ገረመው አባተ    በበኩላቸው ማህበሩ ከአራት ሺህ በላይ ደጋፊ አባላት እንዳሉት አስታውቀዋል።

አዲስ ይፋ የተደረጉት ቁጥሮች የደጋፊ አባላቱን ቁጥር ለማሳደግና ክለቡን መደገፍ ለሚፈልጉ አካላት ባሉበት ቦታ ሆነው የቻሉትን እንዲያግዙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ገቢውን ለመሰብሰብ ከክለቡ ጋር ውሉን የወሰደው የኤፕላስ ካምፓኒ መስራችና ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ አሰፋ ክለቡን መርዳት የሚፈልጉ ደጋፊዎች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሆነው የአቅማቸውን መርዳት የሚችሉ መሆኑን አመልክተዋል።

ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የመግቢያ ትኬት በኦን ላይን የሚገዙበት አሰራር በቀጣይ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም