ሰባት ዓመታትን የፈጀው የኢትዮጵያ የታሪክ ትምህርት ዝግጅት ተሰረዘ

141

ግንቦት 7/2011 በአዲሱ የስርአተ ትምህርት ክለሳ የኢትዮጵያን ህዝብ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴ በሚዳስስ መልኩ  ስካሄድ የነበረው የታሪክ መማሪያ መጽሀፍት ዝግጅት መሰረዙን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው እንዳሉት፤ አሁን  ላይ የሚሰጠው የታሪክ ትምህርት ፖለቲካዊ እይታው ይበዛል።

ይዘቱም የተመረጡ የፖለቲካ ትርክትን ብቻ ማቀፉ የህዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ እሴትን ዘንግቷል ብለዋል ፡፡

ይህም ተማሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ በተዛባ መንገድ እንዲረዱ በማድረጉ አካባቢያዊ አስተሳሰቦች እንዲስፋፉ ምክንያት እንደሆነ ገልጸው፤ ባለፉት 7 ዓመታት የኢትዮጵያ የታሪክ ትምህርት መጻህፍትን ለመከለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በክለሳ ሂደቱ የታሪክ ምሁራንን በማሳተፍ ከተጠናቀቀ በኋላ መጻህፍቱ ለግምገማ ቢቀርቡም የተወሰኑ የብሔር ልሂቃን ባለመስማማታቸው መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

በዚህም አሁን እየተቀረጸ ላለው የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አወዛጋቢ እየሆነ የመጣው የታሪክ ትምህርት በልዩ ትኩረት እንዲሰራም  ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ምሁር ዶክተር ተፈሪ መኮንን፤ “ኢትዮጵያን ያለ ታሪኳ ማሰብ አይቻልም።አሁን ላይ የደረሰችው በታሪክ ውስጥ አልፋ ነው፤ እንደ አለመታደል ሆኖ በሀገሪቱ የታሪክ ትምህርት ተዳክሟል” ነው ያሉት።

“ታሪክ እውቀት፣ መረጃ፣ ትውስታ፣ መማሪያ ነው”። የሚሉት ደግሞ በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ፤ “ታሪክ መማሪያ ብቻ መሆን ሲገባው በእኛ ሀገር ግን ያ አልሆነም፣መንግስት በታሪክ ላይ እጁን ከቷል” ብለዋል።

የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት በሀገሪቱ  ላለፉት በርካታ ዓመታት በሰነድ ተዘጋጅቶ ለትውልዱ እንዲደርስ መደረጉ በኢትዮጵያ ታሪክና በዜጎቿ ላይ ትልቅ ኪሳራ ማስከተሉንም ዶክተር አልማው ተናግረዋል።

ዶክተር ተፈሪ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የታሪክ ትምህርትን መንግስት ካለመቀበሉም ባሻገር አማራጭ የታሪክ ሰነድና አተያይ ባለማዘጋጀቱ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በሌላ በኩል በኢትየጵያ ታሪክ ውስጥ አለመካተታቸውን የሚገልጹ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄያቸው ተገቢነት አለው የሚሉት ምሁሩ የመጻህፍቱን ጉድለት በጥናት መታረም እንዳለበት መክረዋል፡፡

ታሪክን በስነዜጋ ለመተካት መሞከሩን ያነሱት ዶክተር አልማው፤ መንግስት ታሪክ ሳይሆን ቴክኖሎጂን እናስተምር በሚል ያዘጋጀው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ብዙ ውድቀት ማስከተሉን ጠቁመዋል።

በትምህርት ሂደቱ ትውልዱ ሀገሩንና ታሪኩን እንዳያውቅ መደረጉ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዳያሳጣ ስጋታቸውን አንስተዋል።

ለሀገር እድገት፣ ለህዝቦቿ በሰላም መኖር፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ ለማፍራት በተገቢው የታሪክ እውቀት የታነጸ ትውልድ መኖር አለበት የሚሉት ደግሞ ዶክተር ተፈሪ ናቸው።

ዶክተር አልማው በበኩላቸው በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ኢትዮጵያ  ከየት ወደ የት እያመራች እንደሆነ የሚያሳውቅ አንድ ወጥ የታሪክ ሰነድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የስርዓተ ትምህርት ዳይሬክተሩ አቶ እሸቱ፤ የታሪክ ትምህርት ይዘት፣ የትምህርቱ አቀራረብ፣ አካታችነት ጉድለት እንዳይኖረው እየተፈተሸ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን ታሪክ በጥልቀት ለመፈተሽ የሚያስችሉ የቅድመ ጥናት ፕሮጀክቶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው ትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ  ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ትክክለኛ ታሪክ ለማዘጋጀትና ለሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የሚሰጡ የትምህርትና የማጣቀሻ መጻህፍትን ለማዘጋጀት መታቀዱንም ነው ያነሱት፡፡

በይዘቱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ፣ መካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ፣ ከፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች  አኳያ በጥልቀት ተፈትሸው እንዲደራጁ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም