የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ለምርቶቹ ገበያ በማጦቱ በሙሉ አቅሙ እያመረትኩ አይደለሁም አለ

125

ግንቦት 6/2011 በግሪን ሃውስ ቴክኖሎጂና ሌሎች ምርቶች ላይ የተሰማራው የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ በገበያ ችግር ሳቢያ የማምረት አቅሙን እየተጠቀመ አለመሆኑን አስታወቀ፡፡

ለአበባ እርሻ ልማት አገልግሎት የሚሰጠውን የግሪን ሃውስ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚያገለግሉ የጥሬ እቃ ምርቶች ላይ የተሰማራው የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ በገበያ ትስስር ችግር ሳቢያ የማምረት አቅሙን እየተጠቀመ አለመሆኑ ተጠቆመ።

ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅሰው ፋብሪካው በየዓመቱ ማምረት  ከሚገባው እስካሁን ከ25 በመቶ ወይም ከማምረት አቅሙ ሩቡን አልዘለለም ተብሏል።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከአማራ ፓይፕ ፋብሪካና ሌሎች የግልና መንግሰታዊ ባለድርሻ አካላት ጋር በ'ከውጭ ገቢ-ተኪ ምርቶች' ዙሪያ ያዘጋጀው የውውይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ዳውድ ፋብሪካው ወደስራ የገባው ሙሉ በሙሉ የውጭ ምርቶችን በግብአትነት ለሚጠቀሙ የአበባ እርሻ ኩባንያዎች በማቅረብ ገቢ ምርቶችን በአገር በቀል ምርቶች ለመተካት፣በሌላ በኩል ምርቶችን ወደውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ነው።

በዚህም ለአበባና ፍራፍሬ አምራቾች የግሪን ሃውስ ፊልሞች በተጨማሪ ለስኳርና  መስኖ ፕሮጀክቶች የውሃ ማቆሪያ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ  ቱቦዎችን (ፓይፕ) ምርቶችን በማምረት ከውጭ በሚገቡ የግብርና ቴክኖጂዎችን ለመተካት ወደስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ፋብሪካው ግዙፍ ማምረቻ መሳሪዎችን በማስገባትና በዓለም አቀፍ ደረጃ አውቅና ካላቸው ኩባንያዎች የፋብሪካ ጥሬ ዕቃ እየተቀበለ ወደምርት ቢገባም ከታክስና ከምርት ዋጋ ችግር ጋር በተያያዘ ችግር እንዳጋጠመው ነው የገለጹት።

ፋብሪካው በሰዓት 1 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን፣ በዓመት ደግሞ 8 ሺህ 640 ሜትሪክ ቶን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ያለው ምርት የማምረት አቅም ቢኖረውም እስካሁን እያመረተ ያለው ግን ከሚገባው 25 በመቶ አይበልጥም።

ይህ የሆነው ደግሞ ከታክስ፣ ከውጭ ምንዛሬ፣ የምርት ዋጋ መናር፣ ግንዛቤ ፈጠራ ክፍተት፣ የሃይል መቆራረጥ ከችግሮች መካከል ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተለይም ድርጅቱ ከውጭ ጥሬ ዕቃዎችን ሲያስገባ ቀረጥ ስለሚከፍል ምርቶችን ወደገበያ ሲለውጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ስለሚጠይቅ ደንበኞች ከውጭ ከሚያስገቡበት ዋጋ እስከ 20 በመቶ ጭማሪ ዋጋ ይጨምራል ብለዋል።

ለአብነትም በግሪን ሃውስ ፊልም ምርቶችን የሚጠቀሙ የአበባ አምራቾች በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሲባል ከውጭ ከቀረጥ ነጻ ቴክኖሎጂዎችን ስለሚያስገቡ በአገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን በከፍተኛ ዋጋ መገብየት አልቻሉም ነው ያሉት።

አቶ አደም አንደሚሉት ፋብሪካው አገር ውስጥ አምርቶ አገር ውስጥ ሲሸጥ ዋጋው መቀነስ ነበረበት የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ደንበኞች በከፍተኛ ዋጋ ገዝተው ወደ ጭው ለመላክ ችግር ስላለው የአገር ውስጥ ምርቱን ከመጠቀም ከወጭ ለማስገባት ተገደዋል።

እንደ መፍትሄም ድርጅቱ ከውጭ የሚያስገባቸው ጥሬ ዕቃዎች ከቀረጥ ነጻ ቢሆኑ መወዳደርና የምርት ዋጋውን ቀንሶ ለደንበኞች ማቅረብ እንደሚችል ከታክስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መንግስት ማስተካከል እንዳለበት ነው የገለጹት።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ቢሰራ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ገበያም መቆጣጠር እንደሚችል ገልጸው፤ ለዚህም ምርቱን ለተለያዩ ደንበኞች ለማስዋወቅ ድርጅቱ የተለያዩ ዕድሎችን እየተጠቀመ መሆኑን ገልፀዋል።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሐላላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለግብር ምቹ ሆኖ እያለ እድሉን በሙሉ እየተጠቀመች አለመሆኑን ገልጸዋል።

የግሪን ሃውስ ቴክኖሎጂ በጥራታቸውና ዕድገታቸው የሚፈለጉ የግብርና ምርቶችን ለማምረት እንደሚያስችል ገልጸው፤ አማራ ፓይፕ ፋብሪካም ለዚህ ግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በከፍተኛ ጥራትና መጠን የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነ ገልጸው፤ ምርቶቹ ከአፍሪካ ገበያ አልፎ ወደሌሎች የዓለም ክፈሎች የማደግ እድል እንዳለው ጠቁመዋል።

ስለሆነም ፋብሪካው በሚያመርታቸውም ሆነ በሌሎች አገራት ያሉ ተጫማሪ ምርቶች የማምረት ዕድሎች በማስፋት፣ መንግስትም ለግብርና መር ኢኮኖሚው ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

የጥሬ ዕቃም ሆነ በምርቶች ላይ የታክስ ሂደቱን የማጣጣም፣ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የስታንዳርዳይዜሽን ስራዎች መስራት፣ አምራቾችን ማበረታታት ስራዎች እንደሚሰሩ  አረጋግጠዋል።

25 በመቶ አቅሙን መጠቀም ያልቻለው ፋብሪካው ቢያንስ 85 በመቶ አቅሙን አንዲጠቀም ያጋጠሙት ችግሮችን ከባለ ድርሻ ተቋማት ጋር በመሆን ሊፈቱ እንደሚገባ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም