የጥናትና ምርምር ስራዎችን የመጠቀም ልማድ ማስፋት ይገባል ተባለ

108

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2011በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን የመጠቀም ልማድ ማስፋት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርሲስ ዩንቨርስቲ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርሲስ ዩንቨርስቲ መንግስታዊ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን የመጠቀም ልማድ ማስፋት እንደሚገባ ገለጸ።


በዩንቨርስቲው በየዓመቱ የሚዘጋጀው አምስተኛው ብሔራዊ ፐብሊክ ሴክተር ትራንስፎርሜሽንና ልማት የምርምርና ጥናት ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።


የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርሲስ ዩንቨርስቲ በዋናነት የመንግስት ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች የሚያግዙና ሊያዘምኑ የሚያስችሉ ጥናቶችን እያከናወነ ይገኛል።

የሙያቶኞችን አቅም፣ እውቀት፣ ክህሎትና የአመራርነት ስልጠናዎችን እየሰጠ ሲሆን በመደበኛው ትምህርት ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ከ700 ሺህ በላይ ደግሞ አጫጭር ስልጠናዎችን እንዲወስዱ አድርጓል።


የምርምርና ጥናት ስራዎች ገና ጅምር ቢሆኑም እያመጣ ያሉት ውጤቶች ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የመንግስት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንደ ግብዓት መወሰድ አለባቸውም ብለዋል።


ይህም ዩንቨርስቲዎች የሚሰሩትን የምርምር ስራ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት።


የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው የሲቪል ሰርቪስ ሴክተሩ የአገር ልማትን በማሳለጥ በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ሴክተሩ ፖሊሲዎችን በመቅረጽና በመተግባር፣ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ፣ ገቢ በመሰብሰብና ወጪን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም     በግልጽ ማስተዳደር ላይ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።


ይሁንና ሲቪል ሰርቪሱ "አቅመ ቢስና ብቃት የሌለው፣ ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ የሌለው፣ ዝቅተኛ ክፍያና ተነሳሽነት የሚታይበት" መሆኑን ጠቁመዋል።


የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴክተሩ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት በጥናትና ምርምር በመፍታት ለሴክተሩ የሚሰጠውን አሉታዊ አስተሳሰብ መቀየር አለበት ነው ያሉት።


በየምርምርና ጥናት ጉባዔው ከሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ተሳታፊዎች የታደሙ ሲሆን 56 የጥናትና ምርምር ስራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዛሬ የተጀመረው ይሄው ጉባዔ በነገው እለት ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም