የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የግዕዝ ቋንቋን ለማሳደግ የጥናት ማዕከል አቋቁሞ እየሰራ ነው

95

ግንቦት  5/2011 የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የግዕዝ ቋንቋን ለማሳደግ የጥናት ማዕከል አቋቁሞ በዘርፉ የሰለጠኑ ምሁራንን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርስቲው የግዕዝ ቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ትምህር ክፍል ያዘጋጀው የመጀመሪያው የግዕዝ ጉባኤ ዛሬ በባህር ዳር ተካሂዷል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ ችግር ፈች ምርምሮችን ለማካሄድ የግዕዝ ቋንቋን ማወቅ ወሳኝ  ነው።

ለዚህም  ዩኒቨርስቲው የጥናት ማዕከል በማቋቋም  የግዕዝ ቋንቋን ለማሳደግ  ጥረት እያደረገ  መሆኑን ተናግረዋል።

"በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ መጽሃፍትን የማሰባሰብና በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው" ብለዋል።

ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ጉዳዩ ሀገራዊ ስለሆነ ቋንቋውን በስርዓተ - ትምህርታቸው ውስጥ ሊያካትቱት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርስቲው  የቋንቋና ስነ -ጽሁፍ ትምንህርት የግዕዝ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አባ በአማን ግሩም በበኩላቸው

ግዕዝ  ኢትዮጵያዊያን ተመራምረው ታሪክ የሰሩበት የሚስጢር ባለቤት ቋንቋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወጣቱ ትውልድ የጋራ ሃብቱ መሆኑን አውቆ  ተመራምሮ እንደአባቶቹ  የጥበብ አሻራውን ለማሳረፍ የግዕዝ ቋንቅን መማር አለበት።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ካለፈው ዓመት ጀምሮ በግዕዝ ቋንቋ  የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ተቋሙ የቅበላ አቅምን ለማስፋት በዘርፉ ያጋጠመውን የሰለጠኑ መምህራንና የማጣቀሻ መጽሃፍት እጥረት  ለማስተካከል ከትምህርት ዘርፉ አመራሩ የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነም ጠቁመዋል።

"የግዕዝ የታሪክ ድርሳናትን መለስ ብሎ መመርመር ቢቻል ኢትዮጵያዊያን በአራቱም አቅጣጫ እኩል ታሪክ ያላቸውና በደም የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው"ያለው ደግሞ ሙሀዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው።

የግዕዝ ቋንቋ የአንድ ኃይማኖት መገልገያ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ዘር ቀለምና ጎሳ ሳይለዩ ሲመራመሩበትና ታሪካቸውን ሲሰንዱበት እንደነበር አስታውሷል።

ሆኖም በተዛባ አመለካከት ምክንያት  ቋንቋው  እንዲዳከም መደረጉን ዲያቆን ዳንኤል አውስቶ "

በአራቱም አቅጣጫ ያሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች በሁሉም ክፍል የጋራ ታሪክ የሰሩና በጋብቻ ተሳስረው የሚገኙ ናቸው" ብሏል።

ለዚህ ማረጋገጫነቱ ደግሞ የኢትዮጵያን የግዕዝ የታሪክ ድርሳናት በሚገባ መመርመርና ማጥናት እንደሚያስፈልግ አብራርቷል።

መንግስት እንደ ሌሎቹ የሀገሪቱ ቋንቋዎች ሁሉ በስርዓተ ትምህርት ተካቶ እንዲሰጥ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

ጀርመን ከኢትዮጵያ በወሰደቻቸው መጽሃፍት እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ትምህርት እየሰጠች በርካታ ምርምሮችን እያከናወነችበት ነው ተብሏል።

የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ አግልግሎት እንደሰጠ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጉባኤው ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ   የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም