የትግራይ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ግብር መሰብሰቡን አስታወቀ

119

መቐለ ግንቦት 05 /2011 የትግራይ ክልል ገቢዎች ለልማት ባለሥልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ግብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፉ ሊላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፣ገቢው የተሰበሰበው ከ180ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች  ነው።

ከግብር ከፋዮች መካከልም 11ሺህ580 ያህሉ የተጨማሪ እሴት ታከስ(ቫት) ተመዝጋቢዎች ናቸው ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰበሰበው ገቢ የዕቅዱን 74 በመቶ እንደሸፈነም ገልጸዋል።

ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የስድስት በመቶ ያህል ብልጫ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።


የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግንዛቤ መምጣቱን ያመለከቱት ወይዘሮ አሰፉ፣በዚህ ዓመት በየደረጃው የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ  ሳምንትና በትምህርት ቤቶች የተቋቋሙት ክበባት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ በገቢ አሳባሰብ ሂደት ችግር የፈጠሩ 74 ነጋዴዎችን እያንዳንዳቸውን 50ሺህ ብር መቅጣቱን አስታውቀዋል።

በያዝነውና በቀጣዩ ወራት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።

በግብር አከፋፈል አርአያ ከሆኑና በመቀሌ ከተማ ቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ የቢሮና የቤት ዕቃዎችን በመሸጥ የተሰማሩ አቶ ተሰማ ኃይሉ ከገቢያቸው የሚጠበቅባቸውን 65ሺህ ብር ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

''ተገቢውን ግብር ሳንከፍል መሠረተ ልማት መጠየቅ አንችልም።ስለዚህ ከምናገኘው ገቢ ለመንግሥት በመክፈል አርአያ ልንሆን ይገባል'' ብለዋል።

በመቀሌ ከተማ የሃውልት ክፍለ ከተማ በእህል ጅምላ ንግድ ላይ የተሰማሩ ወይዘሮ ሮማን ታደሰ በበኩላቸው፣በዚህ ዓመት 40ሺህ ብር ግብር እንደከፈሉ ገልጸው፣ሌሎችም ግብራቸውን እንዲከፍሉ እየቀሰቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ግብር በወቅቱ በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪና ህጋዊ እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2011 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደው 4ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም