በኦሮሚያ ክልል ዘመናዊ የገበያ ሥርዓትን ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ቢሮው አስታወቀ

54

ነቀምቴ ግንቦት 5 / 2011 ዘመናዊ የገበያ ሥርዓትን በማስፈን ፍትሃዊ የንግድ ተወዳዳሪ ለማድረግ መዘጋጀቱን የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ ፡፡

ቢሮው በነቀምቴ ከተማ በምዕራብ ኦሮሚያ ለስድስት ዞኖችና ለአራት ከተሞች ንግድ ጽህፈት ቤቶች ለሥራ ሂደት አስተባባሪዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የቢሮው አማካሪ አቶ ፊጤ አበራ በዚሁ ጊዜ እንዳስታወቁት የክልሉን የንግድ አሰራርን በማዘመን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል።

ቢሮው አዲስ መዋቅርና አደረጃጀት ዘርግቶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሕገ ወጥ የንግድን መከላከልና አግባብ ካላቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይገኝበታል።

የንግድ ሥራ ፈቃድ አሰጣጥን በኢንተርኔት ማስደገፍ ፣የንግድ ውድድርን ፍትሃዊ ማድረግና የሸማቾችን  መብት ማስከበር  ከተግባራቱ መካከል ናቸው ብለዋል።

በክልሉ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ሕገ ወጥ ንግድ በመስፋፋት በመንግሥት ገቢና በሕዝቡ ኑሮ ተጽዕኖ ማሳደሩን አቶ ፊጤ አስታውቀዋል፡፡

የጅማ ዞን ንግድ ጽህፈት ቤት የንግድ ፍትሃዊነት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሱልጣን አባ ድልቢ በሰጡት አስተያየት በክልሉ የሚታየውን ኋላቀር የንግድ አሰራር በማዘመን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የቄለም ወለጋ ዞን  የንግድ ጽህፈት ቤት የተጠቃሚዎች መብት ጥበቃና የንግድ ውድድር ቡድን መሪ አቶ መልካሙ ማሞ በበኩላቸው በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የተጠቃሚዎችን መብትና ግዴታ ለማስከበርና የንግድ ቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዘመን የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት  እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የንግድ ጽህፈት ቤት የኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ አሰፋ ገመዳ በበኩላቸው የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ  በማፍራትና  ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት  በማስገባት ድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም