የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ የላቀ መሆኑ ተገለጸ

54

ጎንደር ግንቦት 4 / 2011  የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ከመቀነስ አንጻር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ የላቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚድዋይፍ ማህበር አስታወቀ።

"ሚዲዋይፎች የሴቶች መብት ተሟጋቾች" በሚል መሪ ቃል ማህበሩ 27ኛውን አለም አቀፍ የሚድዋይፍ እለት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ዝግጅት አክብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ሚድዋይፍ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካሌ  የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ  ስራዎች የሚድዋይፎች ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ እየተደረገ ባለው ሀገራዊ ጥረት ማህበሩ የበኩሉን እየተወጣ  እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የማህበሩ ፕሬዚደንት እንዳሉት የሰለጠኑ ሙያተኞችን በብዛትና በጥራት ከማፍራት ባለፈ የሚድዋይፎችን አቅምና ብቃት በማሳደግ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ ነው። 

የጎንደር ዩንቨርሲቲ በዘርፉ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን በኩል በሀገሪቱ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

በሀገሪቱ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ ላይ የሚገኙ 12 ሺህ 400 ሚድዋይፎች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ  ዶክተር የቆየሰው ወርቁ በኢትዮዽያ አንዲት ሴት በአማካኝ አምስት  ልጆች እንደምትወልድ ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ከሚገኙ እናቶች 85 በመቶ የሚሆኑት በቤት ውስጥ እንደሚወልዱ አስረድተዋል። 

የጤና ሚኒስቴር ለ20 ዓመታት የሚያገለግል ሀገር አቀፍ የጤና ሴክተር እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተው የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ "የእናቶችና ሕጻናትን ሞት መቀነስ አለም አቀፍ ግዴታ ከመሆኑም ባሻገር የአንድ ሀገር የለውጥና የእድገት መለኪያ መስፈርት ነው" ብለዋል፡፡

ክልሉ በ850 ጤና ጣቢያዎችና በ82 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የወሊድ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም 50 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት የሚወልዱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከ100 ሺህ ነፍሰጡር እናቶች መካከል በወሊድ ወቅት የሚገጥመውን የሞት አደጋ ወደ 200 ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ከማህበሩ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ናቸው።

የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲቻል በአዋላጅ ነርስነት የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎችን ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እያስተማረ መሆኑን አመልክተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ "የሚድዋይፈሪ የሙያ ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታልን ጎብኝተዋል፡፡

ከሀገሪቱ የተለያዩ የጤና ተቋማት የተውጣጡ የማህበሩ አባላት፣ ከፌደራልና ከተለያዩ ክልሎች የተጋበዙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የህክምና ባለሙያዎች በመርሃ ግብሩ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም