ተቋማቱ ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ ተከታታይ መረጃ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል

169

ባህር ዳር ግንቦት 5 /2011 የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ ተከታታይ መረጃ ማድረስ እንደሚጠቅባቸው ተጠቆመ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ አዘጋጅነት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት የንቅናቄ መድረክ ትናንት በደብረ ታቦር ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቦሰና ተገኘ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ግብርናውን ለማዘመንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የተቋማቱ ድርሻ የጎላ ነው።

ለኢንዱስትሪው ዋነኛ ግብዓት የሆነው ግብርና ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ተላቆ ወደ ዘመናዊነት እንዲቀየርም ተቋማቱ አርሶ አደሩን የሚያነሳሱ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በክልሉ በ2011/12 የምርት ዘመን ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉን መሬትም በቆሎ፣ ጤፍና ስንዴን ጨምሮ በዘጠኝ የተመረጡ ሰብሎች በኩታ ገጠም እርሻ ለማልማት ማሳ መለየቱን አስረድተዋል።

በዚህም አሁን 22 ነጥብ 8 በመቶ የሆነውን የክልሉን አማካኝ የሰብል ምርታማነት ወደ 27 ኩንታል ለማድረስ ያስችላል ብለዋል።

የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ አስፈላጊነት ለማሳወቅ እየሰራ መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል።

ከውጭ ግዥ ከተፈፀመው አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እስካሁን ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጠው ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑንም አስረድተዋል።

”ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ መሰረት የሆነውን ግብርና ለማዘመን የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ አላምረው ናቸው።

ክልሉ በሁሉም መስኮች የመልማት ፀጋ ያለው በመሆኑ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን እንዲያሳድግ ዘወትር ማስተማር፣ ማንቃትና ማስገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል።

ምርምሩ የሚያፈልቃቸውንና የሚያላምዳቸውን የሰብል ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ ደርሰው እንዲጠቀምባቸው ማስተማር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መዋቅር ግንባር ቀደም ሆኖ ሊሰራ ይገባል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፈው ጋዜጠኛ ሙላቴ አስማረ በበኩሉ ግብርናውን ለማዘመንና አርሶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራም አስረድቷል።

በክልሉ በ2010/2011 የምርት ዘመን ከለማው መሬት 102 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ እንደተቻለም ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ በአዘጋጀው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን የመኽር ሰብል ንቅናቄ መድረክ ከክልሉ መገናኛ ብዙሃን፣ ከፋና፣ ከኢዜአ፣ ከኮሙኒኬሽን ቢሮዎችና ሌሎች ሚዲያ ተቋማት የተውጣቱ ከ150 በላይ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።