የጤና ተቋማቱ የህክምና አገልግሎት በቅርበት እንድናገኝ አስችሎናል-የዋግ ኽምራ ዞን ነዋሪዎች

66

ሰቆጣ ግንቦት 5 / 2011 በዋግ ልማት ማህበር የተገነቡ የጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት በቅርበት እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ማህበሩ ሰባት ጤና ጣቢያዎችን ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

የዞኑ አንደንድ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳመለከቱት ማህበሩ ያስገነባቸው የጤና ተቋማት ረጅም ጉዞ ከማድረግና ከእንግልት በማላቀቅ በአቅራቢያቸው አገልግሎት ለማግኘት አብቅተዋቸዋል።

የሰላምጌ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሰፉ ግርማይ እንደገለፁት ቀደም ሲል በአካባቢያቸዉ የህክምና ተቋም ባለመኖሩ በሽተኞችን ለማሳከም ሦስት ሰዓት የእግር ጉዞ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተለይም በቀበሌው መንገድ ባለመኖሩም እናቶች በወሊድ ምክንያት ለህመምና ለሞት ሲዳረጉ ነበር ይላሉ፡፡

‘’ከአራት ዓመት በፊት በገጠመኝ ከፍተኛ ምጥ ምክንያት ወደ ማይጨዉ ሆስፒታል ሪፈር ተብዬ በእግር ጉዞ እየሄድኩ በነበርኩበት ሰዓት ከፍተኛ ደም ፈሶኝ ራሴን ስቻለሁ። የልጄም ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል‘’ ብለዋል፡፡

ማህበሩ በአከባቢው ጤና ጣቢያ መገንባቱ ስቃይና እንግልት እንዳስቀረላቸዉ ወይዘሮ አሰፉ ገልጸዋል።

በደሃና ወረዳ ሲልዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዋጋ ጨርቆሴ በበኩላቸው ቀደም ሲል የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የአራት ሰዓት የእግር ጉዞ ያደርጉ እንደነበር አዉስተዋል፡፡

‘’አካባቢያችን ወባማ እንደመሆኑ መጠን በፈለግነዉ ወቅት ህክምና ለማግኘት እንቸገራለን‘’ የሚሉት አስተያየት ሰጪ፣ በተለይም እናቶች በወሊድ ጊዜ ጤና ተቋም ለመድረስ ለእንግልት ብሎም  ለሞት ይዳረጉ ነበር ብለዋል፡፡

የኅብረተሰቡ የጤና ተቋም ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል የሚሉት ደግሞ የቀበሌዋ ነዋሪ አቶ ፋንታዉ የኋላዉ ናቸዉ፡፡

‘’ህመምተኛ ይዘን የስደስት ሰዓት የእግር ጉዞ በመጓዝ ለእንግልት እንዳረጋለን። ህመምተኞችም የበለጠ ስቃይ ይደርስባቸዋል‘’ ሲሉም ያሳለፉትን መከራ አስታውሰዋል፡፡

ማህበሩ ደረጃዉን የጠበቀ ጤና ጣቢያ በአካባቢያችን በመገንባቱ የኅብረተሰቡን እንግልት ማስቀረቱንና ይህም ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል በማለትም ተናግረዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አሳይ ግብረሂዎት በበኩላቸዉ በማህበሩ የተገነቡት ጤና ጣቢያዎች በ21 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ60 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ  ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ተቋማቱን በሰዉ ኃይልና በቁሳቁስ ለማሟላት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ ከደረጃ በታች ያሉ 32 የጤና ኬላዎችንና 10 ጤና ጣቢያዎች መንግስታዊና መንግሰታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተደረገላቸዉ የበጀት ድጋፍ ከ2009 ጀምሮ እየገነቡ መሆናቸዉን የተናገሩት ደግሞ የዋግ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አምላኩ አበበ ናቸዉ፡፡

ከመንግስትና ከአባላት በተገኘ 60 ሚሊየን ብር ድጋፍም አበርገሌ፣ ደሃና፣ ሰሃላ እና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ሰባት ጤና ጣቢያዎችን በዚህ ዓመት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትጤና ጣቢያዎቹ የተሟላ ህክምና እንዲሰጡ ለማድረግ ግብዓትና ቁሳቁስ እየተሟላላቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ከጤና ጣቢያዎች በተጨማሪም በሰቆጣ የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል የጨቅላ ህጻናት ማቆያ ማዕከል ግንባታ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ እስተዳደር ዞን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም