የአብጃታ ሀይቅ በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ዓመታት ሊጠፋ ይችላል---የአብጃታና ሻላ ሀይቆች ብሄራዊ ፓርክ

169

ግንቦት 5/2011 ከአውሮፓና ከኤሲያ ጭምር ለሚመጡ ስደተኛ ወፎችን መጠለያ ሆኖ የሚያገለግለው የአብጃታ ሀይቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየደረቀ መሆኑን የአብጃታና ሻላ ሀይቆች ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ ገለፁ ።

የፓርኩ ሃላፊ አቶ ባንኪ ቡደሞ ለኢዜአ እንደገለፁት ሃይቁ ከአሁን በፊት 194 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የነበረው ሲሆን በአሁን ጊዜ ከግማሽ በላይ በመቀነስ ከ80 ካሬ ኪሎ ሜትር በታች ወርዷል ።

“ጥልቀቱም በአስደንጋጭ ሁኔታ ከ14 ሜትር ወደ 2 ሜትር ዝቅ ማለቱን ሃላፊው ገልፀው በዚሁ ከቀጠለ በሚቀጥሉት አምስት ስድስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ልናጣው እንችላለን” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል  ።

 “ለዚህ ዋናው ምክንያት ወደ ሻላ ሀይቅ የሚፈሱ ገባር ወንዞች በመስኖ ልማት ጫና ፍሰታቸው መቋረጡ ፣በአካባቢው የሚገኘው የሶዳ አሽ ፋብሪካ በቀጥታ በፓምፕ እየሳበ የሃይቁን ውሃ የሚጠቀም መሆኑንና የደን መመናመንን ተከትሎ ሃይቁ በደለል በመጎዳቱ ነው” ብለዋል ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ፓርኩ ክልል እየገቡ መንደር መስርተው መኖር የጀመሩ የአካባቢው ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ አባወራ መድረሱን ገልፀው በፓርኩ ስካውቶች ለመከላከል የተደረገው ጥረት ለሁለት ሰራተኞች  መሞትና ለሰባቱ የአካል ጉየዳት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል ።

የግጭቱ መንስኤ ደን እየጨፈጨፉ ከሰል ማክሰልና አሸዋ ማውጣት እንዲተዉ ሲነገራቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረት ጥቃት ለማድረስ በመነሳታቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

“ሐይቁን መታደግ የሚቻለው በመስኖ ልማት ላይ የተሰማሩ የአበባ ልማቶች ከገባር ወንዝ ይልቅ የከርሰ ምድር ውሃ አበልፅገው እንዲጠቀሙ በማድረግ ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በስፋት ማከናወን ፣ በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት ሆነው ደን ከመጨፍጨፍ እንዲታቀቡና በሃላፊነት መንፈስ ሃይቁን እንዲጠብቁ በማነሳሳት ነው” ብለዋል ።

ለመፍትሔው ተግባራዊነት የምዕራብ አርሲና የምስራቅ ሸዋ  ዞኖች አስተዳዳሪዎች ፣ አባገዳዎች ፣ ቄሮዎችና የሚመለከታቸው አካላት  ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን ኃላፊው በመልካም ጎኑ አንስተዋል ።

የሶዳ አሽ ፋብሪካው ከወንዙ እየሳበ የሚጠቀመውን ውሃ ማቋረጡና ሼር ኢትዮጵያ የተባለ የአበባ ልማት ድርጅት ከቡልቡላ ወንዝ የሚጠቀመው የውሃ መጠን መቀነስ ሓይቁን ለማዳን አጋዥ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ አሳድሯል ።

በአብጃታና ሻላ ሀይቆች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ ፍላሚንጎና ፔሊካን የመሳሰሉት 463 የአእዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ ።

አእዋፋቱ የአብጃታ ሀይቅን የሚመገቡበት የሻላ ሀይቅ ደግሞ የሚራቡበት ቦታ መሆኑን የገለፁት አቶ ባንኪ “በርካታ የኤሲያና የአውሮፓ አእዋፍ ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት የብርድ ወራት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሃይቆቹ ቆይታ ያደርጋሉ” ብለዋል ።

የአርሲ ነገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ አብዶ በበኩላቸው እንደገለጹት ብሄራዊ ፓርኩ በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳቱ በተለይ ደግሞ የአብጃታ ሃይቅ እየደረቀ በመምጣቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በንፋስና በአባሯ እየተጎዱ ነው ።

የወረዳው አስተዳደር ህዝቡን በማስተባበር ብሄራዊ ፓርኩን ለማዳን አስፈላጊው ጥረት እንደሚያደርግ ገልፀው የችግሩ ስፋት ከአካባቢው አቅም በላይ በመሆኑ የፌዴራል መንግስትን ጨምሮ የክልልና የዞን አመራሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።

የነገሌ አርሲ ኡታዋዩ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ቱፋ ደራርሱ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የሚገኙ አባገዳዎች በተጠናከረ መንገድ ህዝቡን በማስተባበር ብሄራዊ ፓርኩን ከመጥፋት ለመታደግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ።

“700 ወጣቶችን በማደራጀት ፓርኩን እየጠበቁና የአካባቢ ጥበቃ ስራን በማከናወን ተጠቀሚዎች እንዲሆኑ አሰማርተናቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል ።

 “የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተስፋ ሰጪ በመሆኑ የመንግስት ድጋፍ ከታከለበት ብሄራዊ ፓርኩን እንደምናድነው እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ አባገዳ ቱፋ ደራርሱ ተስፋቸውን ገልፀዋል ።

አብጃታ ፣ ሻላና  ዝዋይ  የመሳሰሉ ሃይቆች ከደረቁ የስምጥ ሸሎቆ አካባቢ ለእሳተ  ገሞራ አደጋ ሊጋለጥ ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሃሳብ የሰነዘሩት ደግሞ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ ዓሳና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማእከል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ለማ አበራ ናቸው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም