“ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” በሚል አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ሊፈጥሩ ነው

107

አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች “ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” በሚል ውህደት አገራዊ ፓርቲ ለመፍጠር የሚስችላቸውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገለፁ። 

ውህደቱን የፈጠሩት የኢትዮጵያ የሽግግር ምክር ቤት (ሽግግር)፣ ኢትዮጵያችን ህዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን)፣ ቱሳ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ቱሳ)፣ የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኦህዴህ) እና ደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ቅንጅት (አረንጓዴ ኮከቦች) ናቸው።

ፓርቲው የመስራች አባላት ምዝገባን፣ የፖለቲካ ፕሮግራምን፣ መተዳደሪያ ደንብንና ህገ-መንግስታዊና የምርጫ ህጎችን የሚመለከቱ ረቂቆች ማዘጋጀቱ ዛሬ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቅሷል።

መስራች አባላቱ ከሰባት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ መሆናቸው ታውቋል።   

የተዋሃዱ ፓርቲ አመራሮችም ከዛሬ ጀምሮ በፊት የነበራቸው የፓርቲ ስያሜ ከስሞ “ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” በሚል እንዲጠራ መስማማታቸውን ነው የተናገሩት።

በስምምነታቸውም ፓርቲው ሁሉንም አካታች፣ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ፌዴራሊዝም፣ መፈቃቀድና መከባበር እንዲሁም በተባበረና በእኩልነት የተመሠረተች ለሁላችን የምትመች ኢትዮጵያን መመስረት ነው።

ፓርቲዎቹ ከአሁን በፊት በአገር ውስጥና በውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው።

የፓርቲውን ፕሮግራም፣ ርዕዮት፣ ፓርቲውን የሚመሩ አዲስ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የፓርቲው ፍኖቶች አስመልክቶ አባላቱና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት የምስረታ ጉባኤ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ ይሆናል ተብሏል።

ተመሳሳይ የፖለቲካ ርዕዮት ያላቸው ፓርቲዎች ውህደት ፈጥረው ተወዳዳሪና ጠንካራ የፖለቲካ አማራጭ ይዘው እንዲመጡ በቀረበው አገራዊ የውህደት ጥሪን ተከትሎ የተደረገ ሁለተኛው ውህደት ነው።

በተጠናቀቀው ሳምንትም በስድስት ፓርቲዎች ውህደት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መመስረቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም