የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ትናንት ተካሄደዋል

70

ግንቦት 5/2011 የ11ኛው ሳምንት የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በአዲስ አበባና ሮቤ ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ በሶስት የጨዋታ መደብ ተጋጣሚውን ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 0 አሸንፏል።

በትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስ በአምስት የጨዋታ መደብ መከላከያን 3 ለ 2 ማሸነፍ ችሏል።

በክልል ከተማ ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን በሶስት የጨዋታ መደብ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ረቷል።

ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገው የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጣና ባህርዳርን 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የሐበሻ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የውድድር መመሪያ መሰረት አንድ ክለብ 3 ለ 0 ፤ 3 ለ 1 ሲያሸንፍ ሶስት ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን 3 ለ 2 ካሸነፈ ደግሞ 2 ነጥብ ተሸናፊው ክለብ 1 ነጥብ ያገኛል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ28 ነጥብ ሲመራ፣ መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ በ26 ነጥብ፣ ሙገር ሲሚንቶ በ20 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

በፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃ ይዟል።

የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተደርገዋል።

ትናንት ድሬዳዋ ላይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 41 ለ 22 አሸንፏል።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ ያደረጉት ጨዋታ በ22 ለ 22 አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ጎንደር ከተማ ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 20 ለ 18 በማሸነፍ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዘገብ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መከላከያን 34 ለ 22 ሲያሸንፍ ዱራሜ ላይ ፌዴራል ፖሊስ ከምባታ ዱራሜን 31 ለ 30 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ22 ነጥብ ሲመራ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ19 ነጥብ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ16 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም