በሂሳብ ትምህርት መስክ የተሰማሩ ሴቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ተከበረ

765

ግንቦት 5/2011 በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው በሂሳብ ትምህርት መስክ የተሰማሩ ሴቶች ቀን በኢትዮጵያ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካንፓስ በትላንትናው እለት ተከብሯል።

የበዓሉ መከበር ዋነኛ ምክንያት በዓለም ላይ በሂሳብ ትምህርት መስክ  የሴቶችን ተሳትፎ  ለማሳደግ ያለመ ነው።

በሂሳብ ኖቤል ሽልማት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማት ከተቀበሉ ሰዎች የመጀመሪያዋ ሴት ማርያም ሞርዛሆኒ የልደት ቀንን በመዘከር ጭምር ነው እለቱ የሚከበረው።

የበዓሉ መከበር ዋነኛ ምክንያት በዓለም ላይ በሂሳብ ትምህርት መስክ የሴቶችን  ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ነው።

በሂሳብ ኖቤል ሽልማት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማት ከተቀበሉ ሰዎች የመጀመሪያዋ ሴት ማርያም ሞርዛሆኒ የልደት ቀንን በመዘከር ጭምር ነው እለቱ የሚከበረው።

በበዓሉ አከባበር ላይ አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ፣ በሳይንስና፣ ቴክኖሎጂ ሂሳብ ትምህርቶች ላይ የሚሰራው ድርጅት ስቲም ፓወር ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቅድስት ገብረ አምላክን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ሴት መምህራን እንዲሁም ከ1ኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ሴት ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

በሂሳብ ትምህርት መስክ የተሰማሩ አፍሪካዊያን ሴቶች ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጋለም ፀጋዬ በዝግጅቱ መክፈቻ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓለም በዘርፉ ያለው የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር በዓሉ በየዓመቱ እንዲከበር መደረጉን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያም ሴቶች በሂሳብ ትምህርት የመሳተፍ ዝንባሌ እንብዘም ነው ያሉት ዶክተር ይርጋለም “አሁንም ሳይንስ ለሴት አይሆንም” የሚለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ሴቶች ወደ ሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርቶች በብዛት እንዲመጡ ለማበረታታት እለቱን ማሰብ እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

ለተሳታፊዎች ቀርበው የህይወት ልምዳቸውን ያካፈሉት አምባሳደር ገነት ዘውዴ “ሴትና ሳይንስ  አብሮ አይሄድም እየተባሉ” ማደጋቸውንና ለዚህም የማህበረሰብ ሳይንስ ላይ እንዲያተኩሩ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በሳይንስ፣  ቴክኖሎጂና  የሂሳብ  መስኮች  ላይ  የሴቶች  ተሳትፎ ዝቅተኛ  እንዲሆን  ተጽዕኖ መፍጠሩን የገለፁት አምባሳደር ገነት ይህን ሁኔታ ለመለወጥ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል።

ከዘመነ ሳይንስ በፊት ሴቶች ብዙ ሳይንሳዊ ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን እንደሰሩ የተናገሩት አምባሳደሯ ሴቶች  በውስጣቸው ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም አሉታዊ አስተሳሰቦችን በማሸነፍ በሂሳብ መስክ ትምህርቶች ላይ ሊሳተፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ስቲም ፓወር ኢትዮጵያ የተሰኘው በሳይንስና፣ ቴክኖሎጂ ሂሳብ ትምህርቶች ላይ የሚሰራው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቅድስት ገብረ አምላክ በበኩላቸው ሴቶች የፈጠራ ስራ  ሲሰሩ ተጨባጭና ዘላቂ ችግራቸውን ሊፈታላቸው በሚችል መልኩ ነው ብለዋል።

ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሂሳብ  መስኮች  ተማሪዎች  በተግባር  የተደገፈ  ትምህርት  ያገኙ  ዘንድ በተለያዩ  ዩኒቨርሲቲዎች  ማዕከላትን  ገንብቶ  እየሰራ  እንደሚገኝ  አመላክተው  ሴቶች  በመስኩ  የበለጠ  እንዲሳተፉ  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

ድርጅቱ የተማሪዎችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ የሚያስችል  በዩኒሸርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ማዕከላት የመገንባት ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ከዚሁ ፕሮጀክት ተጠቃሚ  እንዲሁኑ ለማስቻል  እንደሚሰራም  አረጋግጠዋል።