የአይላ ጤና ጣቢያ ስራ ባለመጀመሩ አገልግሎቱን በአቅራቢያችን ማግኘት አልቻልንም- ነዋሪዎች

119

ግንቦት 4/2011 በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከሁለት አመት በፊት ግንባታው የተጠናቀቀው የአይላ ጤና ጣቢያ ስራ ባለመጀመሩ አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው ማግኘት እንደተቸገሩ ነዋሪዎች ገለፁ ።

የወረዳው ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት በበኩሉ ጤና ጣቢያው መብራት፣ ውሀና ቁሳቁስ ስላልተሟላለት አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን ገልፆ በዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ስራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል ።

በዙርያ  ወረዳው የውሳሞ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አማኑኤል በየነ ለኢዜአ እንደገለፁት ጤና ጣቢያው ግንባታው  በ2008 ዓም ቢጠናቀቅም እስካሁን ስራ አልጀመረም ።

"እንጠብቅ የነበረውን አገልግሎት በአቅራቢያችን ማግኘት ባለመቻላችን ከሁለት ሰዓት በላይ በእግር በመጓዝ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ ጤና ጣቢያ በመሄድ ለመታከም ተገደናል" ብለዋል ።

መንገዱ ተራራማና ተሽከረካሪ የማይገባው በመሆኑ ህሙማንን በቃቴዛ ተሸክሞ ለማድረስ ከሚደርሰባቸው ድካም ባለፈ የደከሙ ህሙማን በመንገድ ላይ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ተናግረዋል።

"የአይላ ጤና ጣቢያ ግንባታ ሲጀመር ለነዋሪዉ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮ ነበር" ያሉት ደግሞ የጋልአነ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ማርታ ማንቾ ናቸው።

"የጤና ጣቢያው መገንባት በቅርበት ህክምናውን ስለምናገኝ የእናቶችና ህፃናት ሞት ይቀንሳል የሚል ተስፋ ነበረን" ያሉት ወይዘሮ ማርታ ጤና ጣቢያው ከተጠናቀቀ በኋላ ነዋሪው የጠበቀውን አገልግሎት ባለማግኘቱ ቅሬታ እንደፈጠረበት ተናግረዋል ።

የውሳሞ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብርሃም በየነ  በበኩላቸው "ማዞዶይሳ በሚባል ጤና ጣቢያ ሄደን በመታከማችን ለድካም፣ እንግልትና የጊዜ ብክነት  ተዳርገና" ብለዋል ።

"በተደጋጋሚ በሚካሄዱ የህዝብ ውይይት መድረኮች ጤና ጣቢያው ስራ እንዲጀምር ለአስተዳደር አካላት ጥያቄ ብናቀርብም በቅረቡ ስራ ይጀምራል ከሚል ምላሽ ውጭ ተግባራዊ የተደረገ ነገር  ባለመኖሩ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ይስጠን" ሲሉ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ።

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጤና አጠባበቅ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለሙ መንዛ ጤና ጣቢያ ለ25 ሺህ ሰው በቀርበት አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ በ3 ሚሊዮን ብር መገንባቱን ተናግረዋል ።

ግንባታዉ  ከሁለት ዓመት በፊት ቢጠናቀቅም ውሀና የኤሌክትሪክ ስላልገባለት ስራ ሳይጀምር መቆየቱን ጠቅሰዋል ።

የጤና ባለሙያዎች መኖሪያ ቤት ግንባታ በጊዜ አለመጠናቀቅና የቁሳቁስ አለመሟላት ሌሎች ተቋሙ ስራ እንዳይጀምር ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል ።

ለጤና ጣቢያውን በተያዘው ወር መጨረሻ ስራ ለማስጀመር 13 ጤና ባለሙያዎች እንደተመደቡለትና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችና መድሃኒቶች እየቀረቡለት መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ የጤና ባለሙያዎች መኖሪያ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን የኤሌክትሪክና የውሀ አገልግሎቶች እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም