የፓልም ዘይት ለጤና ችግር እንዳያጋልጥ በአግባቡ መጠቀም ይገባል--በዘርፉ የተደረገ ጥናት

143

ግንቦት 4/2011 በተለምዶ የሚረጋው ዘይት እየተባለ የሚጠራው የፓልም ዘይት በጤና ላይ ችግር እንዳያስከትል በብዛትና በተደጋጋሚ አለመመገብ  እንደሚመከር የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ባደረገው ጥናት አመላከተ፡፡  

በኢንስቲትዩቱ የምግብ ሳይንስና ስነ- ምግብ ምርምር ተባባሪ ተመራማሪ አቶ ክፍሌ ሃብቴ የጥናቱን ውጤት መሰረት አድርገው እንዳብራሩት የፓልም ዘይት የሚረጋ የስብ ይዘት ስላለው በብዛትና በተደጋጋሚ መመገብ በሚፈጠረው የኮሎስትሮል ክምችት የደም ስር ቧንቧዎች እንዲጠቡ በማደርግ ለጤና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡

ጉዳቱን ለመቀነስም  ዘወትር ከመመገብ  ይልቅ ከፈሳሽ ዘይት ጋር እያቀላቀሉ ወይም እያፈራረቁ  መጠቀም እንደሚሻል ተመራማሪው ይመክራሉ፡፡

የአለም ጤና ድርጅት መረጃ አንድ ሰው በቀን  ከ50- 70 ግራም  ዘይት  ቢመገብ  ተመራጭ እንደሆነ  ይጠቁማል  ያሉት  የስነ-ምግብ  ተመራማሪው  በኢትዮጵያ  በተደረገ  የምግብ ፍጆታ ጥናት   በአማካይ  28 ግራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አንጻር  ሲታይ  ህብረተሰቡ በአነስተኛ መጠን ስለሚጠቀም  ለችግር ተጋላጭነቱን  እንደሚቀንሰው ያመላከቱት ባለሞያው በብዛት የምንመገብ ከሆነ  የጉዳቱ መጠን ይጨምራል ብለዋል፡፡

የፓልም ዘይት ሙቀትን የመቋቋም አቅም ያለው በመሆኑ በከፍተኛ  ሙቀት ለሚበስሉ ምግቦች  ተመራጭ  ከመሆኑም ባለፈ ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ  የማድረግ ባህሪ  እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የድንች ችብስን  ጨምሮ  በብዛት ለሚዘጋጁ የሆቴል ምግቦች፣  በፋብሪካ  ተዘጋጅተው  ለገበያ  የሚቀርቡ እንደ ብስኩት ያሉ  ምግቦችን ለማዘጋጀት  የፓልም ዘይት  የተሻለ  ነው፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ  ዘይቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው አስገዳጅ የምርት ጥራት ደረጃ ማሟላቱንና የምግብ ደህንነት ስራ አመራር ስርዓት ( ISO 22000) ሰርተፊኬት እንዳለው ተረጋግጦ  በመሆኑ የጤና ችግር እንደማያስከትል ይናገራል፡፡

በአለም የጤና ድርጅት የጥራት ደረጃው የተረጋገጠ መሆኑንና በሌሎች አገራትም ጥቅም ላይ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደሚሉት የሃገሪቱን የዘይት ፍጆታ በሀገር ውስጥ ምርትና በግለሰብ ነጋዴዎች በሚቀርበው ብቻ ማሟላት ስለማይቻል በመንግስት ድጎማ እንደ አማራጭ የሚቀርብ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሶስት አመታት በኋላ መንግስት የፓልም ዘይትን በድጎማ  ማስገባቱን አቁሞ ግለሰብ  ነጋዴዎች እንዲያስገቡ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

የሀገር መውስጥ ምርትን ለማሳደግ በስራ ላይ ያሉ የአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች  የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ማስፋፊያ እንዲያደርጉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ አዳዲስ ባለሃብቶች  ወደ ዘርፉ ሲገቡ  ማበረታቻ እንደሚደረግላቸውም አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት አራት ፋብሪካዎች  በይርጋለም ፣በቡልቡላ፣በጎጃም ቡሬና በአይክር ትግራይ  ግንቧታቸው መጀመሩን አመላክተዋል፡፡

ከ2003-2010  ዓ.ም ድረስ ከ3 ቢሊዮን ዶላር  በላይ ወጭ 2 ነጥብ 93 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የፓልም  የምግብ ዘይት  ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንና  ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ዘይት ፍጆታ በሀገር ውስጥ  የሚመረተው 5 በመቶ፣ በነፃ ገበያ ከውጭ የሚገባ 11 በመቶ እንዲሁም  የፓልም ዘይት 84 በመቶ እንደሚሸፍን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም