ለመንገድ ግንባታ የተቆፈሩ ጉድጓዶች የአደጋ ስጋት መሆናቸውን የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

86

አክሱም ግንቦት 4/2011 በአክሱም ከተማ ለአስፓልት መንገድ ግንባታ ተብለው የተቆፈሩ ጉድጓዶች በመጪው ክረምት አደጋ እንዳያስከትሉ መስጋታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።

የሚመለከተው አካል ችግሩን በመመልከት ለጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልግለትም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል በአክሱም የክንደያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አምለሰት ሃይለ እንዳሉት፣ ለመንገድ ግንባታ ተብለው በሰፈራቸው የተቆፈረ ጉድጓድ ሳይደፈን ለረዠም ጊዜ በመቆየታቸው ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሆኗል።

"በተለይ ልጆችና አዛውንቶች ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው ነው" ያሉት ወይዘሮዋ "ለጎርፍ አደጋ ስጋት ስለሆነ ክረምት ከመግባቱ በፊት ሊደፈኑ አሊያም የመንገድ ግንባታው ሊጠናቀቅ ይገባል" ብለዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሚኪኤለ ተስፋይ በበኩሉ፣በከተማው ውስጥ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ መጀመራቸው ለከተማ እድገትና ለነዋሪዎቿ አገልግሎት አሰጣጥ ምቾት እንደሚፈጥሩ ተናግሯል።

"ነገር ግን ረጅም ርቀትና ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶች የተቆፋፈሩ በመሆናቸው ለጎርፍ ስጋት አጋልጠውናል" ብሏል። 

"የተቆፈሩ ጉድጓዶች ውሃ እያቆሩ ለጎርፍና ሌሎች ተያያዥ ጉዳቶች ስጋት ሆነዋል" ያሉት ደግሞ በከተማው የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተሰፋይ እምባዬ ናቸው።

እየተገነቡ ያሉት መንገዶች የህብረተሰቡ ጥያቄ ሆነው መቆየታቸውንና የከተማው አስተዳደር ተገቢ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ተናግረው፣ ከአክሱም መሰናዶ ትምህርት ቤት ወደ የክንፈ ጎዳና የሚወስድ መንገድ አሁን የተቆፈረ በመሆኑ ለክረምት ጎርፍ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

የመንገዶቹ ጥራት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ አባል አቶ ልጃለም አባዲ እንዳሉት፣ከአደጋ ስጋት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የከተማው ህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የክረምት ወቅት ከመድረሱ በፊት ለመንገድ ስራ የተቆፈሩ ጎድጓዶችን የመድፈን ስራ ይሰራል።

የከተማው የኮንስትራክሽን፣ መንገድና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ገብረአብዝጊ ዮውሃንስ በሰጡት ማብራሪያ፣ የተጀመሩትን የመንገድ ግንባታዎች ክረምት ከመግባቱ በፊት ለማጠናቀቅ በትኩረተ እየተሰራ ነው።

"በከተማው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመምጣቱ የጎርፍ ስጋትን ለመከላከል እና ህብረተሰቡ ለእንቅስቃሴ እንዳይቸገር ተብሎ የተሰራው በጊዜያዊነት የተደፈነው አፈር እና ቦይ ተነስቶ እንደ አዲስ ይሰራል" ብለዋል።

"ከአደጋ ስጋት ጋር ተያይዞ የአከባቢው ማህበረሰብ የሚያነሳው ጥያቄ ተገቢና መለመድ ያለበት ነው" ያሉት ምክትል ሃላፊው በየአከባቢው የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡ የመከታተል ስራ ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሃይሉ በበኩላቸው፣ በሶስት ሳይት የተቆፈሩ የመንገድ ስራዎችን ክረምት ከመግባቱ በፊት ለመድፈን እየተሰራ ነው ብለዋል።

አጠቃላይ በከተማው ውስጥ የ7 ነጥብ አንድ ኪሎሜትር መንገድ ግንባታ በዚህ አመት እንደተጀመረ ስራ አስኪያጁ ተናግረው "የጎርፍ ስጋት ለመከላከል እና የጥራት ችግር እንዳያጋጥም የሙሌት ስራ እየተፋጠነ ነው"ብለዋል።

ቱቦ የመዘርጋት እና አፈር የመድፈን ሥራ በሁሉም ሳይቶች 80 በመቶ መጠናቀቁን የተናገሩት ስራ አስከኪያጁ "የአንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የአስፋልት የማንጠፍ ስራ ከክረምት በፊት ይጠናቀቃል" ብለዋል።

የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀቱ በሁለት አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ስራው በ2011 ዓ.ም.መስከረም ወር ላይ በ280 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተጀመረ ከስራ አስኪያጁ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም