ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት' የሚለውን ስያሜ የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት አልተሰራም

158

 አዲስ  አበባ 4/2011 ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን ለማስተዋወቅ የዛሬ ሁለት አመት ያዘጋጀችው 'ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት' የሚለው ትኩረት ተሰቶ የማስተዋወቅ ሰራ ስላልተሰራበት ውጤታማ እንዳልሆነ ተገለፀ፡፡

ቱሪስት ኢትዮጵያ ድርጅት ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት (Ethiopia Land of origin) የሚለውን በድጋሜ ለመስተዋወቅ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ አካሄዷል፡፡

የቱሪስት ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት  አዲሱን ስያሜ ትኩረት ሰጥተን ባለማስተዋወቃችን ዘርፉ ማምጣት ያለበትን ውጤት አላመጣም ብለዋል፡፡

ዜጎች ስለ ቱሪዝም ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ፣ በግለሰቦች እጅ የሚገኘውን የቱሪስት መስህብ ለደበኞች ክፍት አድርጎ አገልግሎት እንዲሰጥ አለመስራቱና የመሳሰሉት ደግሞ ዘርፉ በታሰበው ልክ ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉት ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ለደንበኞቻችን አለን ብለን ቃል የገባንላቸው መሬት ላይ አለመገኘት፣ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን በመጤ ባህሎች መመረዛቸውና የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታም ተግዳሮት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ዜጎች ስለ አገራችን ተፈጥሮ ሐብትና ሰው ሰራሽ ቅርሶች በቂ ግንዛቤ አግኝተው ቅርሶችን በመጠበቅና በመስተዋወቅ ለትውልድ በማስተላለፍ አገራችን የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን በመስራት የዜግነት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

መስሪያ ቤቱ ችግሮችን ለመፍታት አዲሱን የቱሪዝም መለያ ለማስተዋወቅ በዓለምና አገር አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም ትኩረት ሰጥተን በማስተዋወቅ ቱሪስቶችንና ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ውስጥ በመምጣት ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያመጣ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በዚህም ረጅም ጊዜ የወሰደ ጥናት ተጠንቶ ችግሮች ተለይተው መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በቱሪስት ኢትዮጵያ ድርጅት የገቢያ ትውውቅ ቡድን መሪ አቶ ወልደገብሬል በርኼ በበኩላቸው አዲሱን የቱሪዝም መለያችንን ለማስተዋወቅ የትርጓሜ ክፍተት፣ የመረጃ አያያዝ ክፍተት፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሀገራችን ባህልና እሴትን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት አለመስጠት በታሰበው ልክ እንዳይሰራ አድርጎታል ብለዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ልጅ ዘር መገኛ መሆኗን ፡የስልጣኔ መነሻ፡ የቡና፣ የጤፍ ፡የእንሰት፡የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች መገኛ መሆኗን ተረድተው የበኩላቸውን መስራት እንደለባቸውም ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የምትታወቅበት የ13 ወራት ፀሐይ ብርሃን (13 month of sunshine) የቱሪዝም መለያ ነበራት፡፡ ይህም በወቅቱ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ አሁን ደግሞ ወቅቱ የሚጠብቀውን መስፈርትና የደበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ 'ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት' (Ethiopia Land of origin) የሚል መለያዋን እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም