በመሠረተ ልማት አስፈፃሚ ተቋማት የሚታየውን ብክነትንና የአገልግሎት ችግሮችን ለማስቀረት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ተባለ

56

ጋምቤላ ግንቦት 3 / 2011 የመሠረተ ልማት አስፈፃሚ ተቋማት የሀብት ብክነትንና የአገልገሎት መቋረጥ ችግሮችን ለማስቀረት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

በመሠረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራርና በካሳ ዓዋጅ አፈፃፀም ዙሪያ ያተኮር ውይይት በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በመድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት እንዳሳሰቡት የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ፣ የውሃና የቴሌኮም መሠረተ ልማት አስፈፃሚ ተቋማት የሀብት ብክነትና የአገልግሎት መቋረጥ ችግሮች ለማስቀረት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ አብርሃም ሻሜቦ በሰጡት አስተያየት ቅንጅታዊ አሰራር ባለመኖሩ በሀገር ሀብት ላይ እየደረሰ ካለው ኪሳራ በተጨማሪ በአገልግሎት ላይም ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተለይም በመሠረተ ልማት ተቋማት መካከል ተቀናጅቶ ለመሥራት ባለመቻሉ አንዱ የሰራውን ሌላው በማፍረስ እየደረሰ ያለው ብክነትንና የአገልግሎት መስተጓጎል መፍትሄ እንዲፈለግለት አሳስበዋል።

የመሠረተ ልማት አስፈፃሚ ተቋማት ተቀናጅተው ባለመስራታቸው በአገር ሀብት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት ደግሞ ሌለው ተሳታፊ አቶ ትንሳኤ ራንጃን ናቸው።

በመሆኑም ተቋማቱ በመቀናጀት ብክነትንና የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር ማስቀረት አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጋምቤላ ሪጅን ተወካይ አቶ ዘላለም ብርሃኑ እንደሚሉት ችግሩን ለማስቀረት ከተቋማቱ ቅንጅታዊ አሰራር ባለፈ ከተሞች የተቀናጅ መሪ ፕላን ሊኖራቸው ይገባል።

በተለይም በጋምቤላ ከልል የሚገኙ አብዛኛዎቹች ከተሞች መሪ ፕላን የሌላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሮቹ እየተስተዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተንኳይ ጆክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የመሠረተ ልማት  አስፈፃሚ ተቋማት ባለመቀናጀታቸው ፕሮጀክቶች እየተጓጓተቱ ነው ይላሉ።

የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ምክትል ዳሬክተር ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር እንደተናገሩት የመሠረተ ልማት አስፈፃሚ ተቋማት በቅንጅት ባለመስራታቸው በአገር ሀብት ከሚደርሰው ጉዳት ባለፈ፤ ሕዝቡ አገልግሎቶች እየተቋረጡበት ነው ።

ከዚህም በተጨማሪ ለልማት ተነሺዎች ወጥነት ያለው የካሳ አከፋፈል ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ከልማት በሚፈጠር ውዝግብ ፕሮጀክቶች በተያዘላችው የጊዜ ሰሌዳ እየተፈጸሙ ያለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ በካሳ አከፋፈል ላይ ያለውን የግንዛቤ የማሳደግና ወጥነት ያለው አፈፃፀም በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያልተቀናጀ የመሠረተ ልማት አገልግሎት ችግር ለዘመናት ያልተፈታ ችግር ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም