ኮሚሽኑ አሰራሩን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የተላበሰ ለማድረግ እየሰራሁ ነው አለ

62

አዳማ ግንቦት 3 /2011አሰራሩን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የተላበሰ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተቋሙ አዳዲስ አሰራርንና አደረጃጀትን በመፈጠር ለደንበኞች ፈጣን፣ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት  በመሥራት ላይ ነው።

ኮሚሽኑ በዘርፉ የሚታየውን የሰነድና የንግድ ምልክት ማጭበርበር፣የወጪና ገቢ ዕቃዎች ቅሸባና ሕገ  ወጥነት ለመቆጣጠር አዳዲስ የፍተሻ ጣቢያዎችና ኬላዎችን እያደራጀ መሆኑን አመልክተዋል።

የጉምሩክ አስተላላፊዎችን ጨምሮ በየደረጃው ያሉት የተቋሙን ባለሙያዎችና አመራሮች የማጥራትና በአዲስ መልክ በመመደብ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ተቋሙ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የመከላከል አቅሙ ማደጉንም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በዚህም የጦር መሣሪያና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሚበዙባቸው የመግቢያና መውጫ በሮች  ክትትልና ቁጥጥሩ መጠናከሩን አመልክተዋል።

እስካሁን በርካታ የጦር መሣሪያዎች በተለይም የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ደበሌ ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ ከአገር ለመውጣትና በቦሌ ዓለም አቀፍ አወሮፕላን ማረፊያ ጭምር ወደ አገር ውስጥ ሊገባ የነበረውን ህገ ወጥ የውጭ ገንዘብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የቁጥጥር ሥራ በመጠናከሩ የመከላከል አቅሙ አምና ከነበረው 16 በመቶ ወደ 33 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ፣ከገቢና የወጪ ዕቃዎች ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

በቀጣይም ህገ ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያዎች ዝውውርንና ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ ለመግታት በእቅድና በሕግ የተደገፈ ሥራ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ የፈጥኖ ደራሽ ኦፖሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር አንሻ ቶላ በበኩላቸው በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠሩ ያሉትን ሕገ ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያዎች ዝውውር እንዲሁም ሕገ ወጥ ንግድ ለመግታት ጥረቱ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የለውጡ ፈተና እየሆነ ያለው ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሕገ ወጥ ንግድ ነው ያሉት ኮማንደር አንሻ፡ ይህን ከምንጩ ለማድረቅ የሕግ ማስከበር ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ብለዋል።

የፍትህና ፀጥታ አካላት ወንጀል ለመከላከል እያሳዩ ያሉት ቁርጠኝነት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችና ሕገ ወጥ  እንቅስቃሴን ከመግታት አንፃር የተሻለ አፈፃፀም እየታየበት መሆኑን አስረድተዋል።

መልኩን እየቀያየረ የመጣውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ቡሬ፣ዛለአንበሳንና ራማን ጨምሮ በ94 የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ኮማንደር አንሻ ገልጸዋል።

ለገቢዎች ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ የተዋቀረው ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 884 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም