በሐረር ከ300 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ ከሚገነቡት ገበያ ማዕከላት 10ሩ ለአገልግሎት በቁ

78

ሐረርግንቦት 3/2011 በሐረር ከተማ ከ300 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጭ እየተገነቡ ካሉት የገበያ ማዕከላት አሥሩ ለአገልግሎት መብቃታቸውን የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

ማዕከላቱ በአንድ ማዕከል የተለያዩ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስችሉ ባለቤቶቹ ተናግረዋል። 

የክልሉ የከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱማሊክ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከላቱ እየተገነቡ ያሉት በተለምዶ ሸዋ በርና ሲጋራ ተራ የገበያ ሥፍራዎች ነው።

የማዕከላቱን ግንባታ የሚያከናውኑት በሥፍራው በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረታቸው የወደመባቸው ነጋዴዎች ለክልሉ መንግሥት ያቀረቡትን የመልሶ ማልማት ጥያቄን መነሻ መሆኑንም አስረድተዋል።

ማዕከላቱ ሥራ የጀመሩት በዘጠኝ ማህበራት ለተደራጁ ነጋዴዎችና በስድስት ባለሀብቶች እየተገነቡ ካሉት ባለስምንት ፎቅ 15 ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቀሪዎቹ ማዕከላት ግንባታ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ አቶ አብዱልሃኪም አስታውቀዋል።

ማዕከላቱ ማስተር ፕላኑን መሠረት አድርገው በመገንባታቸውን ለከተማዋ ውበት ከመሆናቸው ባለፈ ፤ ነዋሪዎች ግብይትን በአንድ ማዕከል ለማከናወን እንደሚያስችሉ ኃላፊው ገልጸዋል።

የማዕከላቱ ህንጻ ግንባታ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ቡሌ ቶቶባ ማዕከላቱ እየተገቡ ያሉበት ቦታ ለንግድ ሥራ አመቺ ባለመሆኑ ለሶስት ጊዜ ያህል የእሳት ቃጠሎ የደረሰበትና ንብረት የወደመበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ማዕከላቱ ለገበያተኛውና ለነጋዴዎች አመቺ መሆናቸውን የገለጹት ሊቀመንበሩ "ግንባታው ከማንኛውም አደጋ ስጋት ነጻ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

የገበያ ቦታ አጥተው የነበሩ ነጋዴዎችን በማዕከላቱ በኪራይ መጠቀም እንደሚችሉም አስረድተዋል።

የሐረር አንድነት ገንዘብና ቁጠባ ማህበር ጸሐፊ አቶ አብደላ ቱሴ በበኩላቸው ከአሁን ቀደም በሥፍራው በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቃጠሎ ንብረት እንደወደመባቸው አስታውሰዋል።

ግንባታው ከ100 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ  ሥራ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በከተማ በሦስት የንግድ ስፍራዎች በ2003 እና በ2006 በደረሱ የእሳት አደጋዎች ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት መውደሙ ይታወሳል።

ሐረር ከእንድ ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች ከተማ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም