የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት በመሪዎች መለዋወጥ የሚዋዥቅ አይደለም -አምባሳደር መለስ አለም

133

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2011 የኢትዮጵያና ኬንያ ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በመሪዎች መለዋወጥ የማይዋዥቅ መሆኑን በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም ተናገሩ። 

በናይሮቢ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ከኬንያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኬቲኤን "ቦተም ላይን አፍሪካ" በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ትላንት ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው ይህንን የገለጹት።

በዚሁ ወቅት በሁለቱ አገራት ጥምረት የተቋቋመው የሰላም ኮሚቴ ጠንካራ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ማህበረሰቦች መካከል ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ስለተከሰተው ግጭት ተጠይቀው በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ሁለቱ ህዝቦች ከአንድ ትውልድ በላይ ለዘለቀ ጊዜ አብረው የኖሩና እንደ አንድ ቤተሰብ የሚቆጠሩ ናቸው።የዚህ አይነት አጋጣሚ ከግጦሽ ሳር፣ከውሃ እና ከከብቶች መቀማማት ጋር በተያያዘ በአካባቢው የሚፈጠር የተለመደ ግጭት ነው።

የህዝቦቹ ዋነኛው ችግር በልማት ወደ ኋላ መቅረታቸው ነው ያሉት አምባሳደሩ የችግሩን ምንጭ ከስሩ ማድረቅ የሚቻለው ልማትን በማስፋፋት ብቻ መሆኑንንም ጠቁመዋል።

በአካባቢው በመከናወን ላይ የሚገኘው የላፕሴት ፕሮጀክት የአካባቢውን የመሰረተ ልማት ግንባታ በማስፋፋት ህዝቦቹን የመንገድ ፣የወደብና የባቡር መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ያደርጋልም ብለዋል።

ተከስቶ የነበረው ግጭት የሁለቱን ህዝቦች ጠንካራና ባህላዊ ትስስር የማያሳይና ያላቸውን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሰላማዊ ግንኙነት አይወክልም ሲሉ ተናግረዋል።

 ሁለቱን አገሮች በፅኑ ያስተሳሰሯቸው በድንበር አካባቢ የሚኖሩት ተመሳሳይ ህዝቦች እንደሆኑና የቦረና፣ ገብራ፣ ቡርጂ ህዝቦችን በምሳሌነት ይጠቀሳሉ"

ህዝቦቹ የሚከተሉት አንድ አይነት ባህልና የኑሮ ልማድም ግንኙነቱን አጠናክሮታል ብለዋል።

በአገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ለቀጠናው ምሳሌ የሚሆንና ከ50 አመታት በላይ የዘለቀ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያጸናው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዘመናት ያለፉት የሁለቱ አገራት መሪዎቸም ምንም አይነት የፖለቲካ አመለካከት ቢከተሉም የነበራቸው ትስስር ጥብቅ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያና የኬኒያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከ50 በአመት ላይ የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም