ማዕከሉ በ34 ሚሊዮን ብር ወጪ በተተከለለት ዘመናዊ የማሰራጫ መሣሪያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

70

ጎንደር ግንቦት 3/ 2011 የጎንደር ትምህርት በሬዲዮ ስርጭት ማዕከል በ34 ሚሊዮን ብር ወጪ የተተከለለት ዘመናዊ የማሰራጫ መሣሪያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ላለፉት 22 ዓመታት ያገለገለው ማዕከሉ በመሳሪያዎች ብልሽትና እርጅና ላለፉት ሦስት አመታት ስርጭቱን አቋርጦ ነበር፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት እሸቱ ማዕከሉ ዳግም ወደ ሥራ መግባቱን ለማብሰር በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የመሣሪያው ወጪ የተሸፈነው በአማራ ክልል መንግሥት ነው፡፡

በ972 መካከለኛ ሞገድ የሚሰራጨው መደበኛ የሬዲዬ ትምህርት ፕሮግራም ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በደቡብ፣በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ባሉ የትምህርት ደረጃዎች በአማርኛ ፣ በሳይንስ ፣ በኅብረተሰብ በሥነ-ዜጋና በእንግሊዝኛ የትምህርት ዓይነቶች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የጎልማሶች ትምህርትን ጨምሮ በኤች አይቪ ፤ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መከላከል በንቃተ ሕግ፣ በግብርናና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያዳብሩ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን እንደሚያሰራጭ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በማሰራጫ መሳሪያዎች እርጅናና በመለዋወጫ እጦት ላለፉት ሦስት አመታት የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት አቋርጦ እንደነበረም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ አቶ በየነ መረሳ በበኩላቸው ማዕከሉን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት  በፍላሽና በሚሞሪ አማካኝነት ይሰጥ የነበረውን ፕሮግራም በቀጥታ ስርጭት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

በስርጭት ጣቢያው ለ10 አመታት ያገለገሉት አቶ ንጉሱ ክብረት ማዕከሉ ከሬዲዮ ትምህርት በተጓዳኝ ኅብረተሰቡን የሚያስተምሩና የሚያዝናኑ ፕሮግራሞችን ለአየር በማብቃት አንጋፋ የሬዲዮ ማሰራጫ ማእከል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ስርጭቱ ላለፉት ሶስት አመታት መቋረጡ የማዕከሉን የማደግና የመለወጥ አቅም የተፈታተነ በመሆኑ ወደፊት እንዳይቋረጥ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ያሉት የማዕከሉ አማተር አገልጋይ የነበሩት ወይዘሮ ትዝታ በጋሻው ናቸው፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የትምህርት ስርጭት ማዕከላት ሃላፊዎችን ጨምሮ ከአራቱ ዞኖች የተጋበዙ የትምህርት ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም አማተር አገልጋዮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም