ሆስፒታሉ ለ400 ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አደረገ

53

አምቦ ግንቦት 2 ቀን 2011  የአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል በዓይን ሞራ ግርዶሽ ለተጠቁ 400 ሰዎች ነፃ የቀዶ ጥገና ህክምና መስጠቱን አስታወቀ። 

በተደረገላቸው ህክምና የዓይን ብርሀናቸው መመለሱን ታካሚዎች ገልጸዋል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪጅ አቶ ደበበ ፈጠነ ለኢዜአ እንደገለፁት የቀዶ ህክምናው የተሰጠው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍልና ሂማሊያን ካታራክት ፕሮጄክት በተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት የገንዘብና የባለሙያ ትብብር  ነው።

ሕክምናው ከምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ፣ ጅባት፣ ደንዲ፣ ድሬ ኢንጪኒ፣ ቶኬ ኩታዬና አምቦ ወራዳዎች ለተውጣጡና ከፍለው መታከም ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች  መሰጠቱን ተናግረዋል።

የሂማሊያን ካታራክት ፕሮጄክት አስተባባሪ አቶ አሳሳኽኝ ንጉሴ" ከፍለው መታከም የማይችሉ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂዎችን ከዓይነ ስውርነት ለመታደግ ህክምናው ተሰጥቷል" ብለዋል ።

የኖኖ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አቦነሽ መንግስቱ የአንድ ዓይናቸውን ብርሃን ካጡ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው አስታውሰዋል።

ሁለተኛው አይናቸውም ካለፈው ዓመት ጀምሮ እይታው እየቀነሰ በመምጣቱ  በሰዎች እርዳታ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ተናግረዋል።

"አምቦ ሆስፒታል መጥቼ በተደረገልኝ ህክምና የሁለቱም ዓይኖቼ ብርሀን በመመለሱ ተደስቻለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

በአምቦ  ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃኔ ሰለሞን "አንድ ዓይኔ ማየት ካቆመ ሁለት ዓመት ሆኖታል" ብለዋል።

ከፍለው መታከም ባለመቻላቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት ታማሚዋ፣"በሆስፒታሉ መጥቼ ዛሬ ህክምናውን በማግኘቴ ያጣሁትን የዓይኔን ብርሃን መልሼ አግኝቻለሁ" ብለዋል፡፡  

ከጅባት ወረዳ ነዋሪው አቶ አበበ መኮንን በበኩላቸው በህክምናው ዕይታቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ህክምናውን ላደረጉላቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም