በጤና ባለሙያዎች የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ነው

221

ግንቦት 2/2011 በጤና ባለሙያዎች የተነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በቅደም ተከተል ምላሽ የመስጠት ስራ መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን የጤና ባለሙያዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ መንግስት እየሰጣቸው ያሉ ምላሾችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጤና ባለሙያዎች በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር በነበራቸው ውይይትና ከዚያ በፊት ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎች እንደየቅደም ተከተላቸው ምላሽ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና አገልገሎት ጥራት የአሰራር መመሪያ ክፍተት ከደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ጋር በተገናኘ ባለሞያዎቹ በዋናነት ያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ 3 ሺህ 800 ስፔሻሊስት ሃኪሞች ሁለተኛ  ዲግሪያቸውን እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው በትምህርት በሚኖራቸው ቆይታ የተመደበላቸው በጀት ከየመጡበት ክልል የሚሸፈን በመሆኑ በነበሩበት የህክምና ተቋም ትርፍ በጀት ባለመኖሩ አዲስ ቅጥር ለመቅጠር አዳጋች ሆኖ መቆየቱንም አብራርተዋል።

ችግሩን ለመፍታት የስፔሻሊስት ሃኪሞቹን ደሞዝና ጥቅማጥቅም በዓመት ግማሽ ቢሊዬን ብር እንደሚደርስ ገልጸው ከግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም  ሙሉ ክፍያቸው በፌዴራል መንግስት እንዲሸፈን ተደርጎ ክልሎች የነሱን በጀት ለአዲስ ቅጥር እንዲያዛውሩ መደረጉን አክለዋል።

ይህም በየአመቱ የሚቀጥል በመሆኑ በክልሎች ላይ ያለውን ጫና በማስቀረት በህክምና  ተቋም የሚስተዋለውን የባለሙያ እጥረት ችግርን እነደሚቀርፍ ይናገራሉ።

ቀደም ሲል በመንግስት ብቻ ይሰጥ የነበረው የስፔሻላይዜሽን ስልጠና በአሁኑ ወቅት መስፈርቱን የሚያሟላ ባለሙያ በግሉ ስፔሻላይዝድ ማድረግ የሚችልበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።

በዋናነትም በባለሙያዎች ላይ ይደረግ የነበረውን አስገዳጅ ምደባም እንዲሁ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ማቆሙን ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎች በፈቀዱትና በተመቻቸው የጤና ተቋም ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት አግባብ መፈጠሩን ጠቁመው ይህም እንደ አገልገሎት የሚያዝላቸው ይሆናል።

በተጨማሪም በአስገዳጅ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡና ይህንን ካላደረጉ እስከ 180 ሺህ ብር ይደርስ የነበረው የአስገዳጅ የክፍያ ስረአትም እንዲቀር መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ማንኛውም የጤና ባለሙያ እንደተመረቀ የትምህርት ማስረጃው ተሰጥቶት እንደማንኛውም የትምህርት ዘርፍ የወጪ መጋራት ክፍያ ብቻ ሲያጠናቅቁ ኦርጅናል ማስረጃቸውን መውሰድ እንዲችልም ተመቻችቷል።

በግል የጤና ተቋም የሚማሩ ኢንተረን ተማሪዎችም እንዲሁ በመንግስት ሆስፒታል ተመድበው እንዲሰሩና ወርሃዊ ደሞዛቸውን የሚመደቡበት የጤና ተቋም እንዲከፍላቸው ተወስኗል።

ከደሞዝና ከጥቅማጥቅም ጋር ለተነሳው ጥያቄ አገሪቱ አሁን ያለችበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ደሞዝ ለመጨመር የማያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

ጥቅማጥቅምንና የትርፍ ጊዜ ክፍያን በሚመለከት ግን በ2005 ዓ.ም የወጣና በተለያዩ ምክኒያቶች ተግባራዊ ያልተደረገው መመሪያ እንዲተገበር በእቅድ በተያዘው መመሪያ ምላሽ እንዲያገኝ ይደረጋል።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተጨማሪ በጀት እንዲመደብ ተደርጎ እስከ 25 በመቶ የጤና ባለሙያዎችን ቅጥር በመፈጸም የባለሙያ እጥረትና የስራ አጥነት ላይ ለሚነሳው ጥያቄም ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

ከመመሪያና ከአሰራር ክፍተቶች ጋር በተያያዘ ለሚነሳ ቅሬታ የጤና ፖሊሲው ክለሳ እየተደረገበት መሆኑን አብራርተው ማሻሻያ የሚደረግባቸውን በመለየት የሚስተካከል ይሆናል ብለዋል።

በተለይም አዲሰ አበባን ጨምሮ በክልሎችና በወረዳዎች ላይ ያለው የጥቅማጥቅምና የትርፍ ሰአት ክፍያ ወጥ አለመሆንም በባለሙያው ዘንድ ቅሬታን መፍጠሩን የገለጹት ሚኒስትሩ የአከፋፈልና የታክስ አቆራረጡ በሁሉም ባለሙያዎች ዘንድ እኩል እንዲሆን ከግንቦት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።

በዚህና ሌሎቸ ጉዳዮች ለሚፈጠር የጥራት መጓደል በህክምና በጤና ትምህርት ተቋማት የተሟላ ግብአት አለመኖር እንደምክንያትነት ይጠቀሳል ያሉት ዶክተር አሚር የግብአት አቅርቦት ላይ ፈጣንና ወቅታዊ ለማድረግ ማስተካከያ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዋናነትም የህክምና መሳሪያና የመድኃኒት ግዥ ቀደም ሲል የተንዛዛና ውስብስበ አሰራር እንደነበረው አስታውሰው ለግዥ በዓመት እስከ 170 ጨረታዎች ወጥተው ከስምንት እስከ አስራ ስምንት ወራት ጊዜ ሂደትም ነበረው።

በመሆኑም የግዥ ስርአቱን ለማሳጠር የማእቀፍ ግዥን እንደ መፍትሄ በመውሰድ በፌደራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደር እየተተገበረ በመሆኑ ከግዥና ከጥራት ጋር የሚነሱ ቅሬታዎች ይፈታሉ ብለዋል።

የጤና ትምህርት ተቋማት የመቀበልና የግብአት አቅማቸው ባለመመጣጠኑ እየተፈጠረ ያለውን የጥራት ችግርም ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ተውጣጥቶ የተቋቅመው ኮሚቴም ባለሞያዎቹ ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም