ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ በረከት ስምኦንን መቃወሚያ ውድቅ አደረገ

65

ግንቦት 2/2011 በጥረት ኮርፖሬት የሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።

በቀረበባቸው ክስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ሲሉ  አቶ በረከት ስምኦን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ የቀረቡት አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ታደሰ ካሳና  አቶ ዳንኤል ይግዛው ያቀቡትን የክስ መቃዎሚያዎች በሙሉ ውድቅ ሆነዋል፡፡

አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጥረት ኮርፖሬትን በበላይነት በሚመሩበት  ወቅት ለስራ በማያመች ሁኔታ በመምራት በህዝብ ሃብትና ንብረት ጉዳት ላይ አድርሰዋል በሚል አራት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የክሱን ይዘት ሚያዝያ 14 /2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት በንባብ የተሰማ ሲሆን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል ለዛሬ ቀጠሮ ተይዞ መቆየቱ ይታወሳል።

የቀረበባቸውን ክስ የተቃወሙት ተከሳሾቹ “ጥረት ኮርፖሬት በፌዴራልና ከክልሉ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የሚንቀሳቀስ ድርጅት በመሆኑ ጉዳያችን መታየት ያለበት  በፌዴራል ፍርድ ቤት ነው” ሲሉ ተቃውሞ አቅርበዋል።

“የተከሰስነው ስራ ላይ ባልዋለ ህግ ነው፡፡ወንጀሉ ተፈፀመ የተባለው ከ2007 ዓ.ም በፊት ሲሆን የተከሰስንበት ህግ ግን ከዚያ ወዲህ የወጣ ነው” በማለት ሦስቱም ተከሳሾች በጋራ ተቃውመዋል፡፡

3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ይግዛው በበኩላቸው በግላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት  “ክሱ ተዘርዝሮ አልቀረበም፣ የተድበሰበሰና ግልፅነት ይጎድለዋል” በሚል ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም ከ1ኛና 2ኛ ተከሳሽ ጋር ተጣምሮ መከሰስ የለብኝም፣ በግልፅ የሚያሳይ ተገቢ ማስረጃ የለሌለ በመሆኑም ልከሰስ አይገባኝም በማለት ክሱን ተቃውመዋል፡፡

“አሜሪካዊ ዜግነት ያለኝ በመሆኑ ጉዳዩ በፌደራል ፍርድ ቤት ሊታይ ይገባል” ሲሉም  አቅርበዋል፡፡

አቃቢ ህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ ጉዳያችን በፌደራል ይታይልን ብለው ባቀረቡት ተቃውሞ ጥረት የክልሉ ህዝብ ሃብት መሆኑን ጠቅሶ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በውክልና ጉዳዩን ማየት ይችላል”ብሏል፡፡

“አቶ ዳንኤል ይግዛው የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ቢሆንም ወንጀሉ የተፈፀመው በዚሁ  ክልል በመሆኑ ጉዳዩን በክልል ደረጃ ማየት ይቻልል” ብሏል፡፡

በስራ ላይ ባልዋለ ህግ ነው የተከሰስነው ለሚለው ተቃውሞም ወንጀሉ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ተያያዥነት ያለው በመሆኑ የህግ አንቀፁ ችግር የለበትም ሲል” ተከራክሯል።

ከ1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ጋር ተጣምሮ ክስ መመስረት የለበትም በሚል ላቀረቡት ተቃውሞም የሙስና ወንጀሉ በጋራ የተፈፀመና ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ተለይቶ የሚቀርብ  አለመሆኑን ጠቅሶ አቃቤ ህግ የቀረበውን መቃወሚያ እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ በበኩሉ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ግለሰብም ሆነ  አጠቃላይ የክስ ጉዳዩ በህገ-መንግስቱ መሰረት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማየት ስልጣን እንዳለው አስታውቋል፡፡

በስራ ላይ ባልዋለ የወንጀል አንቀፅ ተከሰናል የተባለውም ክሱ እስኪመሰረት ጉዳዩ ያላለቀና የተገናኘ በመሆኑ ተቃውሞው ተቀባይነት የለውም ሲል ውድቅ አድርጎታል፡፡

በመሆኑም አቶ በረከት የቀረበባቸውን ክስ እንዳልተቀበሉና ወንጀለኛም እንዳልሆኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲያቀርቡ አቶ ታደሰ ካሳ ደግሞ “በቀረበው ክስ ዙሪያ አሁን ላይ  የእምነት ክህደት ቃል መስጠት አልችልም” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ከህግ ባለሙያ ጋር ተመካክረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲያቀርቡ  ለግንቦት 5/2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

በዱቤት ዊንድ ቴክኖሎጂ የተከሰሱት አቶ ዳንኤል ይግዛው በበኩላቸው ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ በጠበቃቸው አማካኝነት የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ቢሆንም በመጭው ሰኞ በዝርዝር እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

ተከሳሾቹ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል አራት ክስ  የተመሰረተባቸው መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም