የምስጥ ኩይሳዎች ለእርሻ ስራችን ፈተና ሆነዋል…በምስራቅ ሸዋ ዞን የዱግዳ ወረዳ አርሶ አደሮች

225

ግንቦት 2/2011 በምስራቅ ሸዋ ዞን በዱግዳና ቦራ ወረዳዎች በሚገኙ የእርሻ ማሳዎች ላይ በብዛት የሚታዩ የምስጥ ኩይሳዎች በምርትና ምርታማነት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ገለፁ ።

ከሞጆ ወደ ሀዋሳ በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ዳር በሚገኙ የዱግዳና የቦራ የእርሻ ማሳዎች ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኩይሳዎች ቆመው መመልከት የተለመደ ነው ።

አንዱ ኩይሳ በውስጡ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ምስጦች እንደሚፈለፈሉበትና ከስሩ ነቅሎ ለማውጣት እስከ ሶስት ሜትር ድረስ በጥልቀት መቆፈር እንደሚጠይቅ የዱግዳ ወረዳ አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ባቲ አቡ ይገልፃሉ ።

ኩይሳዎቹ የእርሻ ማሳ ከማጣበብ ባሻገር በውስጡ የሚፈለፈሉ ምስጦች የተዘራውን ሰብል ስሩን በመብላት በተለይ ደግሞ የታጨደ ነዶና ክምር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ እንደሚያደርጉት አቶ ባቲ ተናግረዋል ።

“ምስጦቹ አደገኞች ናቸው” ያሉት አቶ ባቲ ሰክሮ እመንገድ ላይ የተኛ አንድ ግለሰብ ሌሊቱን ሙሉ ጋቢውን በልተው ጨርሰውት ማደራቸውንም ለአብነት ገልፀዋል ።

በዱግዳ ወረዳ ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አማን ገላሴ እንደገለፁት ደግሞ ኩይሳዎቹ በውስጣቸው ለቁጥር የሚታክት የምስጥ ብዛት አቅፈው የያዙ ናቸው ።

“በወረዳው ከሚገኙ 35 ቀበሌዎች መካከል በ32 ቀበሌዎች የተስፋፉት ኩይሳዎች የእርሻ ማሳዎችን ከማጣበብ ባሻገር ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎችን በትራክተር ለማረስና በኮምባይነር አጭዶ ለመውቃት እንቅፋቶች ናቸው”ብለዋል ።

በምስጦቹ ምክንያት በተለይ ነዶና ክምር ከሁለት ሌሊት በላይ በማሳ ላይ ማቆየት እንዳማይቻል ባለሙያው ገልፀው “የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እየተጎዳ ነው” ብለዋል።

ኩይሳዎቹ አማራጭ ቴክኖሎጂ ካልተፈለገላቸው በስተቀር በአርሶ አደሩ አቅም ከስር ነቅሎ ማጥፋት የማይታሰብ መሆኑን አስረድተዋል ።

በዱግዳ ወረዳ የኦዶ ቦቆ ነዋሪ አርሶ አደር ዶኒ አቡ ኩይሳም ለዓመታት መፍትሄ ያላገኘ የአርሶ አደሩ ችግር መሆኑን ተናግረዋል ።

“በኩይሳው ውስጥ የሚኖሩ ምስጦች የሰብል ምርትን ከማጥፋታቸው በላይ የእንጨት ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስር በልተው በመጣል ኑሮአችንን እያመሰቃቀሉት በመሆኑ መፍትሄ ቢፈለግልን መልካም ነው” ብለዋል ።

አርሶ አደር ገና ዋሪ በበኩላቸው ህዝብ እየበዛ የእርሻ ማሳ ደግሞ እያጠረ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ኩይሳዎች መሬትን እየተሻሙ የበለጠ እያጠበቡት ስለሆነ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል ።

የአካባቢው አርሶ አደሮች የሚያነሱት ቅሬታ መፍትሔ እንዲፈለግለት ለሚመለከተው አካል ደጋግመን እናቀርባለን ያሉት የወረዳው የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የስራ ሒደት ባለቤት አቶ ባቲ አቡ ናቸው።