ኢትዮጵያ የጥጥ ልማት አቅሟን እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ተገለጸ

146

ግንቦት 2/2011 ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት አመቺ ስነ-ምህዳር ቢኖራትም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ የምታመርተው ከእምቅ ሃብቷ ከ4 በመቶ ያነሰ ብቻ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ።

ለጥጥ ልማቱ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ባለመሆኑ በምርታማነታችን ላይ ተጽእኖ ፈጥሮብናል ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ገልጸዋል።

በወረር ግብርና ምርምር ማእከል ብሄራዊ የጥጥ ማስተባበሪያ ተመራማሪ አቶ ዶኒስ ጉርሜሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓለም የጥጥ ምርት የአራተኛ ደረጃ ከያዘችው ፓኪስታን የሚመጣጠን አመቺ የእርሻ መሬትና ተስማሚ የአየር ፀባይ ቢኖራትም የምታመርተው በጣም ዝቅተኛ ነው።

ብቸኛው የጥጥ ምርምር የሚያካሄደው የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ላለፉት 53 ዓመታት ባካሄደው ምርምር በሽታን የሚቋቋሙና የተሻለ ምርት የሚሰጡ 35 የጥጥ ዝርያዎችን ቢያወጣም አባዝቶ ለአምራቾች የሚያከፋፍል አካል ባለመኖሩ በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ሆነዋል ለማለት እንደማያስደፍር ተመራማሪው ተናግረዋል ።

ከዚህ የተነሳም እየተሰበሰበ ያለው የጥጥ ምርት ሃገሪቱ ካላት እምቅ አቅም ውስጥ ከአራት ከመቶ የማይበልጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

“በ2008 ዓ.ም ብቻ እንኳን በሄክታር ከ39 እስከ 46 ኩንታል ድረስ ምርት የሚሰጡ ወረር 50 ፣ ወይጦ 07 እና ሲሲ ኩክ 02 የተባሉ ምርጥ የጥጥ ዝርያዎች ፀድቀው የወጡ ቢሆንም በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ወደ አምራቹ መድረስ አልቻሉም”ብለዋል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርምሩን የሚያስተባብር ክፍል የራሱ የሆነ የሰርቶ ማሳያ መሬትም ሆነ ላባራቶሪ የሌለው በመሆኑና በአቅም ግንባታ ረገድም ትኩረት ስለማይሰጠው ስራውን በብቃት ማከናወን እንዳልተቻለ ተመራማሪው አቶ ዶኒስ ጉርሜሳ ገልፀዋል ።

ለአንዳንድ የጥጥ ምርምሮች ናሙና እየወሰደ ቃሊቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ላባራቶሪ በመጠቀም የአቅሙን ያክል ከመፍጨርጨር የዘለለ ተግባር ማከናወን እንደተሳነውም ከተመራማሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

“በመካከለኛው አዋሽ አካባቢ 120 ሺህ ሔክታር መሬት በጥጥ ሰብል እየለማ እንደነበር የገለፁት ተመራማሪው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አምራቾች በቂ ትኩረትና እገዛ ስለማያገኙ የጥጥ መሬታቸውን ወደ ሸንኮራ አገዳና ሙዝ እየቀየሩት ስለሆነ በጥጥ የሚለማው መሬት ከ70 ሺህ ሔክታር አይበልጥም” ብለዋል ።

በአካባቢው 1ሺህ 200 ሔክታር መሬት ላይ ጥጥ እያለሙ የሚገኙት ባለሃብት አቶ አህመድ መሃመድ በበኩላቸው ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ባለመሰጠቱ የሚጠቀሙት የጥጥ ዝርያ ከ40 ዓመት በፊት የተለቀቀና ምርታማነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል ።

ነባሮቹ ዝርያዎች አቅማቸው እየተዳከመ በመምጣቱ ምርታማነታቸው ከ60 እና 50 ኩንታል ቀስ በቀስ ወደ 34 ኩንታል ዝቅ ማለቱን ባለሃብቱ አስረድተዋል ።

“በአካባቢው የነበረው የመንግስት የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ በመበላሸቱ ምክንያት ያመረትነው የጥጥ ክምችት ለብልሽት እየተዳረገብን ነው” ሲሉም ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።

የምርምር ማእከሉ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ የሚሄድ ምርምር በማካሄድ እንዲያግዛቸውም ባለሃብቱ ጠይቀዋል ።

“የጥጥ ምርት በቀላሉ በተባይና በአረም የሚጎዳ በመሆኑ ተገቢው ፀረ -አረም ኬሚካል በወቅቱ የምናገኝበትና የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ በአካባቢው እንድናቋቁም መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻችልን እንፈልጋለን” ብለዋል ።

በአሚባራ ወረዳ በ86 ሔክታር መሬት ጥጥ በማልማት ላይ የሚገኙት ሌላው ባለሃብት አቶ ደምለው ገበየሁ በበኩላቸው የዘርፉ ዋነኛ ችግር የተሻሻለ ዘርና የፀረ-ተባይ ኬሚካል ነው ።

እስከ አሁን ድረስ አንድ ዓይነት የጥጥ ዝርያ ብቻ እንደሚቀርብላቸው ገልፀው ይሔም ከአካባቢው ጋር በመላመዱ በሔክታር የሚሰጠው ምርት ከ40 ኩንታል ወደ 34 ኩንታል እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀዋል ።

ዘርፉ እንዲጠናከር ከተፈለገ የተሻሻሉ ዝርያዎችና በቂ ኬሚካል ሊቀርብ እንደሚገባም ባለሃብቱ ጠቁመዋል ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መገርሳ ስለሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት መልስ በአምራቾች በኩል የቀረበው ቅሬታ ትክክል ነው።

“ለዚህ ምክንያቱ የጥጥ ልማቱ አንዴ በግብርና ሚኒስቴር ሌላ ጊዜ ደግሞ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር ሲደረግ የቆየና ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ባለቤት ያልነበረው በመሆኑ ነው”ብለዋል።

“አሁን ግን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መስራች ዘሩን ከወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ወስዶ በአሶሳ አካባቢ እንዲባዛ እያደረገ በመሆኑ መፍትሔ ያገኛል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም